ኢራናውያን በአደጋ የሞቱትን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ተተኪ እየመረጡ ነው
አራት ተፎካካሪዎች እየተሳተፉበት ያለው ምርጫ ውጤት ከሁለት ቀናት በኋላ ይገለጻል ተብሏል

ተመራጩ ፕሬዝዳንት የ85 አመቱን አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ተተኪ ስለሚጠቁም ትልቅ ትርጉም ተሰጥቶታል
ኢራናውያን በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ያለፈውን ኢብራሂም ራይሲ የሚተካ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ድምጻቸውን መስጠት ጀምረዋል።
ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የቴህራን አጋሮች የፍልስጤሙ ሃማስ እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በቀጠለበት ወቅት ነው እየተካሄደ ያለው።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ “የኢራን እስላማዊ አብዮት ጥንካሬ፣ ክብር እና ዝና እንዲቀጥል ዜጎች በነቂስ በመውጣት ድምጻቸውን ሊሰጡ ይገባል” ብለዋል።
ሃሚኒ ከቀናት በፊትም በስም ያልጠቀሷቸውን እጩ ተፎካካሪዎች “ከጠላት (አሜሪካ) ጋር ግንኙነት አላቸው” በሚል ኢራናውያን እንዳይመርጧቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለመሳተፍ 80 እጩዎች የተመዘገቡ ሲሆን፥ 12 አባላት ያሉት የጋርዲያን ካውንስል የስድስቱን አጽድቋል።
ሁለቱ እጩዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎም ኢራናውያን ዛሬ ድምጽ የሚሰጡት ለሶስት ወግ አጥባቂ እና አንድ ለዘብተኛ እጩ ነው።
የፓርላማ አፈጉባኤውና የቀድሞው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሃላፊ ሞሃመድ በከር ቃሊባፍ እና የቀድሞው የኒዩክሌር ተደራዳሪ ሳኢድ ጃሊሊ ከአያቶላህ ሃሚኒ ጋር ቅርበት ያላቸው ናቸው።
ብቸኛው ለዘብተኛ እጩ መሱድ ፐዝሽኪያን ሲሆኑ፥ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በ2015 ወደተፈራረመችው የኒዩክሌር ስምምነት እንድትመለስና ከምዕራቡ አለም ጋር ዳግም መቀራረብ እንድትጀምር አደርጋለሁ ሲሉ ቀስቅሰዋል።
በምርጫው በምዕራባውያን ማዕቀብ የተጎዳውን የቴህራን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተሻለ ፕሮግራማቸውን ያስተዋወቁ ተፎካካሪዎች የተሻለ መራጭ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ከሁለት ቀናት በኋላ ውጤቱ ይገለጻል የተባለው ምርጫ ከ1989 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉትን አያቶላህ አሊ ተተኪ ያመላክታል ተብሏል።
በምርጫው አሸናፊ የሚሆነው የትኛውም ተፎካካሪ በኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራም ላይም ሆነ ቴህራን በመካከለኛው ምስራቅ በምትደግፋቸው ታጣቂዎች ዙሪያ አዲስ የፖሊሲ ለውጥ ይዞ ይመጣል ተብሎ አይጠበቅም።
አራቱም የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪዎች በማዕቀብ የተዳከመውን የኢራን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና ሙስናን ለመዋጋት ቃል መግባታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።