ኢራናውያን “የሀገሪቱን ጠላቶች ለማሸነፍ” በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በነቂስ ሊሳተፉ ይገባል - ሃሚኒ
የሃይማኖታዊ መሪው ዜጎች ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን እጩዎች እንዳይመረጡም ጥሪ አቅርበዋል
ኢራን የፊታችን አርብ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኢብራሂም ራይሲ የሚተካ ፕሬዝዳንት ይመርጣሉ
ኢራናውያን “የሀገሪቱን ጠላቶች ለማሸነፍ” በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በነቂስ በመውጣት ድምጽ እንዲሰጡ የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ አሳሰቡ።
ሃሚኒ በስም ባይጠቅሷቸውም ሁሉም መልካም ነገር ከአሜሪካ ይገኛል ብለው የሚያምኑና በምርጫው የሚሳተፉ ፖለቲከኞችንም አውግዘዋል።
የ69 አመቱ የልብ ቀዶ ህክምና ባለሙያ መሱድ ፕዜሽኪያን በሃይማኖታዊ መሪው ከተወገዙት መካከል አንዱ እንደሚሆኑ ተገምቷል።
ፕዜሽኪያን ኢራን ከአሜሪካ ጋር በ2015 ወደተፈራረመችው የኒዩክሌር ስምምነት እንድትመለስና ከምዕራቡ አለም ጋር ዳግም መቀራረብ እንድትጀምር ጥሪ አቅርበዋል።
ሃሚኒ “ለአሜሪካና እስራኤል ሞት” በተመኙበት ንግግራቸው “ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ያለአሜሪካ ይሁንታ በኢራን እድገት ማስመስገብ ይቻላል ብለው የማያምኑ ሰዎች አይበጇችሁም” ሲሉ ኢራናውያን ድምጽ እንዳይሰጧቸው አሳስበዋል።
ኢራን የፊታችን አርብ በግንቦት ወር በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኢብራሂም ራይሲ የሚተካ ምርጫ ታካሂዳለች።፡
በምርጫው በምዕራባውያን ማዕቀብ የተጎዳውን የቴህራን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተሻለ ፕሮግራማቸውን ያስተዋወቁ ፖለቲከኞች የተሻለ መራጭ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
በሃሚኒ ትችት የተሰነዘረባቸው መሱድ ፕዜሽኪያን በህዝብ ዘንድ እምብዛም የሚታወቁ ባይሆኑም በቴህራን እና ሌሎች ከተሞች ባደረጓቸው የምርጫ ቅስቀሳዎች በርካታ ደጋፊ ማግኘታቸው ተዘግቧል።
ተጠባቂው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ85 አመቱን አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ተተኪን የሚወስን ነው።
አምስት ወግ አጥባዊና አንድ ለዘብተኛ እጩዎች የሚፎካከሩበት ምርጫ የሃሚኒ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ እጩ እንደሚያሸንፉበትም ይጠበቃል።
የፓርላማ አፈጉባኤውና የቀድሞው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሃላፊ ሞሃመድ በከር ቃሊባፍ እና የቀድሞው የኒዩክሌር ተደራዳሪ ሳኢድ ጃሊሊ ከአያቶላህ ሃሚኒ ጋር ቅርበት ያላቸው ናቸው።
አማካሪዎቻቸውም መራጮች ከሃሚኒ ጋር ያልተቃረነ ሃሳብ ያለውን እጩ እንዲመርጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።