የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ “ቁድስ ሃይል” መሪ ኢስማኤል ቃኒ ሳይገደሉ አልቀረም ተባለ
በአሜሪካ የተገደሉትን ቃሲም ሱሊማኒ የተኩት ኢስማኤል ቃኒ ባለፈው ሳምንት በቤሩት ከታዩ በኋላ ደብዛቸው መጥፋቱ ተነግሯል
የቴህራንን የውጭ ሀገራት ወታደራዊ ተልዕኮዎች የሚፈጽመው “ቁድስ ሃይል” መሪው ሄዝቦላህን ለማገዝ ሊባኖስ ገብተው ነበር ተብሏል
የኢራን አብዮታዊ ዘብ “ቁድስ ሃይል” መሪው ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኤል ቃኒ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ እየተነገረ ነው።
ኒውዮርክ ታይምስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን የኢራን ምንጮቹን ጠቅሶ ለመጨረሻ ጊዜ ከአንድ ሳምንት በፊት በቤሩት የታዩት ኢስማኤል ቃኒ በእስራኤል የአየር ጥቃት ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ዘግቧል።
ከእስራኤል ከፍተኛ ጥቃት ሲደርስበት የነበረውን ሄዝቦላህ ለመርዳት ወደ ሊባኖስ ያቀኑት ቃኒ የሄዝቦላህ ቀጣዩ መሪ ይሆናሉ ከተባሉት ሳየድ ሰይፈዲን ጋር መምከራቸው ተገልጿል።
እስራኤል ሁለቱ መሪዎች የሚመክሩበትን የምድር ውስጥ መደበቂያ መደብደቧን ተከትሎም ህይወታቸው ሳያልፍ እንደማይቀር ተገምቷል።
የእስራኤል ጦርም ሆነ ኢራን ግን ስለሄዝቦላህ አዲስ መሪ እና የቁድስ ሃይል መሪው መጥፋትም ሆነ መገደል እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
የእስራኤሉ ታይምስ ኦፍ እስራኤል በቤሩት የሚገኙ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላትን ዋቢ አድርጎ ቴህራን በኢስማኤል ቃኒ ዙሪያ እስካሁን ዝምታን መምረጧ ድንጋጤ መፍጠሩን አስነብቧል።
ኢራን በውጭ ሀገራት የምታካሂዳቸውን ተልዕኮዎች የሚፈጽመውና የአብዮታዊ ዘቡ ዋነኛ ደጀን ተደርጎ የሚቆጠረው “ቁድስ ሃይል” መሪው ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኤል ቃኒ በርግጥም ከተገደሉ በእስራኤል ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ሁለተኛው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ መሪ ይሆናሉ።
ቃኒ የተኳቸው ቃሲም ሱሌማኒ በጥር ወር 2020 በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ በኢራቅ መዲና ባግዳድ መገደላቸው ይታወሳል።
በኢራን ለተፈጸመባት የሚሳኤል ጥቃት አጻፋውን እንደምትመልስ የዛተችው እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃቷን ቀጥላለች።
ቴል አቪቭ በደቡባዊ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሯን አስገብታ ከሄዝቦላህ ጋር ውጊያ ከጀመረች ወዲህም 440 የቡድኑን ተዋጊዎች መግደሏን ነው ያስታወቀችው።
ባለፉት ቀናት ከተገደሉት ውስጥ 30ዎቹ በተለያየ እርከን የሚገኙ የሄዝቦላህ አዛዦች መሆናቸውን የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ ተናግረዋል።
በደቡባዊ ሊባኖስ የተጀመረው የእግረኛ ጦር ውጊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንን ያፈናቀለ ሲሆን፥ የጋዛ አይነት ውድመትን እንዳያስከትልና ቀጠናዊ ጦርነት እንዳይቀሰቅስ ስጋት ፈጥሯል።