ኢራን ወደ ሶሪያ ወታደሮችን ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀች
የሶሪያ አማጺ ቡድኖች ሃማ የተሰኘችውን ከተማ ከበሽር አል አሳድ ጦር ለማስለቀቅ መቃረባቸው ተገልጿል
ኢራን እና ሩሲያ በሶሪያ የዘጠኝ አመት የእርስ በርስ ጦርነት ከአሳድ ጎን መሰለፋቸው ይታወቃል
ኢራን ወደ ሶሪያ ወታደሮችን ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አል አረቢያ አል ጃቤድ ከተሰኘ የኳታር መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የሶሪያ መንግስት ጥያቄ ካቀረበ ኢራን ወታደሮችን እንደምትልክ ተናግረዋል።
ቴህራን በሶሪያ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዳግም የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማርገብና ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ እየተዘጋጀች መሆኑንም ነው የገለጹት።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው "ሃያት ታህሪር አል ሻም" የተሰኘውና ሌሎች አማጺ ቡድኖች በኢድሊብ ግዛት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መጠነሰፊ ማጥቃት ጀምረዋል።
የአሌፖ ከተማን ተቆጣጥረው የሶሪያ መንግስት ጦርን ከከተማዋ ያስወጡት አማጺያን ሃማ የተሰኘችውን ከተማ ለመያዝ መቃረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
"የሽብር ቡድኖቹ ግስጋሴ ከኢራን በበለጠ እንደ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ እና ቱርክ ካሉ የሶሪያ ጎረቤቶች ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል" ያሉት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፥ ከቱርክ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብም ቴህራን ማሸማገል ትችላለች ብለዋል።
ኢድሊብ ሩሲያ ባደራደረችው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ከ2020 ጀምሮ በቱርክ ሃይሎች ጥበቃ እየተደረገላት ነው።
ሩሲያ፣ ቱርክ እና ሶሪያ የመንግስታቱ ድርጅት በሶሪያ ተኩስ እንዲቆምና ፖለቲካዊ ሽግግር ለማምጣት በሚል በ2015 ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ ለማስፈጸም በ2017 በካዛኪስታን መዲና አስታና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
የአስታናው ስምምነት ሶስቱ የሀገራት የጋራ የቁጥጥር ግብረሃይል በማቋቋም ለሶሪያ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያበጁ ቢያዝም አፈጻጸሙ ላይ ክፍተት እንዳለ ይነገራል።
ቴህራንም የቱርክ ወታደሮች ከሶሪያ ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ የጠየቀች ሲሆን፥ የሶሪያ ህዝቦች ህጋዊ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የምትለው አንካራ ግን ጥያቄውን ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ቱርክ የሶሪያን ብሄራዊ አንድነት እና የግዛት ሉአላዊነት እንደምታከብር ጠቅሰው ጦርነቱ እንዲቆም ግን የሀገሪቱን ህዝቦች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሃካን ፊዳን በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ላገረሸው ግጭት ተቃዋሚዎች የሚያነሱት ህጋዊ ጥያቄ አለመመለስን በምክንያትነት አንስተዋል።
ቴህራን ግን የአማጺያኑ ጥቃት የእስራኤል እና አሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን የማተራመስ እቅድ አካል አድርጋ እንደምትመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራጋቺ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ በወቅታዊው የሶሪያ ግጭት ዙሪያ ከሌላኛዋ የአሳድ ደጋፊ ሩሲያ ጋር ለመምከር ወደ ሞስኮ እንደሚያቀኑ መናገራቸውን አርቲ አስነብቧል።