የሶሪያ አማጺያን የአሌፖ ከተማ አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጠሩ፤ የሀገሪቱ ጦር ከከተማዋ ወጥቷል
ሩሲያ የበሸር አል አሳድ መንግስት ጦርን በአየር ጥቃት እያገዘች ትገኛለች

አሜሪካ በበኩሏ ሶሪያ የሩሲያና ኢራን ጥገኛ መሆኗና ለፖለቲካዊ ንግግር ዝግጁ አለመሆኗ ችግሩን አስቀጥሎታል ብላለች
የሶሪያ አማጺያን የአሌፖ ከተማን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠራቸው ተነገረ።
ሃያት ታህሪር አል ሻም (ኑስራ ፍሮንት) የተሰኘው ቡድን ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በፈጸመው ጥቃት 20 ንጹሃንን ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የበሽር አል አሳድ መንግስትን የሚቃወመው ኑስራ ፍሮንት በአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቱርክ እና ሌሎች ሀገራት በሽብርተኝነት ተፈርጇል።
ከ2020 ወዲህ ጠንካራ ነው የተባለው ጥቃት የሶሪያ መንግስት ጦር ከአሌፖ እንዲወጣ ማስገደዱ ተገልጿል።
የበሽር አል አሳድ አጋር የሆነችው ሩሲያም በቡድኑ ላይ የአየር ጥቃት እየፈጸመች መሆኑን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሬውተርስ ሁለት የሶሪያ ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ እንዳስነበበው ሞስኮ በሶስት ቀናት ውስጥ ለደማስቆ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከቱርክ እና ኢራን አቻዎቻቸው ጋር ሶሪያ ዳግም ደም አፋሳሽ ወደሆነ ጦርነት እንዳትመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች መክረዋል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የአማጺያኑ ጥቃት የእስራኤል ኣና አሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን የማተራመስ እቅድ አካል ነው ማለታቸውንም የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሶሪያ ዳግም ያገረሸውን ጦርነት በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ያለችው አሜሪካ በበኩሏ ሶሪያ የሩሲያና ኢራን ጥገኛ መሆኗና ለፖለቲካዊ ንግግር ዝግጁ አለመሆኗ ችግሩን አስቀጥሎታል ብላለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ሲን ሳቬት በአሌፖ ከተማ የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ የጠየቁ ሲሆን፥ በ2015ቱ የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ፖለቲካዊ ድርድር እንዲጀመር አሳስበዋል።
የመቶ ሺዎችን ህይወት ቀጥፎ ሚሊየኖችን ያፈናቀለው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በሩሲያ እና ኢራን ድጋፍ የአሳድ መንግስት አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል እንዲቆጣጠር በማድረግ ከአመታት በፊትጋብ ቢልም ፖለቲካዊ ስምምነት አልተደረሰም።
በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባት የአሌፖ ከተማ በ2016 በሶሪያ መንግስት ጦር መያዟ የአማጺያኑን እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበረው።
"እኔ የአሌፖ ልጅ ነኝ፤ ከስምንት አመት በፊት (በ2016) ነበር ከከተማዋ የተፈናቀልኩት፤ ፈጣሪ ይመስገን አሁን ተመልሻለሁ፤ በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው" ብሏል አሊ ጁማ የተሰኘው የአማጺ ቡድኑ አባል።
የሶሪያ ጦር አብዛኛው የአሌፖ ከተማ ክፍል በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ያረጋገጠ ሲሆን፥ ጦሩ ለመልሶ ማጥቃት ለመዘጋጀት ከከተማዋ መውጣቱ ተዘግቧል።
በሶሪያ የሚንቀሳቀሰው የኩርድ ታጣቂ ቡድን "ዋይፒጂ"ም የሶሪያ ጦር መውጣትን ተከትሎ ይዞታውን እያሰፋ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።