የልብ ቀዶ ጥገና ሀኪሙ መሱድ ፔዝሽኪያን የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
ፔዝሽኪያን ቴህራን ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነቷን ማደስ እንድትጀምር እሰራለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል
በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኣኢብራሂም ራይሲ ለመተካት የተካሄደው ምርጫ አነስተኛ መራጭ የተመዘገበበት ነው ተብሏል
በኢራን አስቸኳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለዘብተኛው መሱድ ፔዝሽኪያን አሸነፉ።
የ69 አመቱ የልብ ቀዶ ጥገና ሀኪም ከ30 ሚሊየን መራጭ የ16 ሚሊየኑን ድጋፍ ማግኘታቸውን የሀገሪቱ የምርጫ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሞህሰን ኢስላሚ ተናግረዋል።
ወግ አጥባቂው ሳኢድ ጃሊሊ በበኩላቸው 13 ሚሊየን ድምጽ ማግኘታቸው ተጠቁሟል።
ፔዝሽኪያን ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ቢያሸንፉም አብላጫ ድምጽ ማግኘት ባለመቻላቸው በትናንትናው እለት ከፍተኛ ድምጽ ካገኙት ጃሊሊ ጋር ዳግም ተፎካክረው ነው ያሸነፉት።
የቀድሞው የኢራን የጤና ሚኒስትር በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው ድጋፍ የሰጧቸውን ኢራናውያን አመስግነዋል።
“ሁላችንም በወንድማማችነት መንፈስ ለጋራ ሀገራችን እድገት እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።
በህዝብ ዘንድ እምብዛም የማይታወቁትና ለዘብተኛ አቋም የያዙት ፔዝሽኪያን ኢራን ወደ 2015ቱ የኒዩክሌር ስምምነት እንድትመለስና ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነቷን እንድታድስ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።
ይህም በአያቶላህ አሊ ሃሚኒ ጭምር መነቀፉ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኢብራሂም ራይሲ ለመተካት በሚደረገው ምርጫ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል የሚል ስጋት ፈጥሮ እንደነበር ፍራንስ 24 አስታውሷል።
የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሃሰን ሮሃኒ እና ሞሀመድ ካታሚ የሰጧቸው ድጋፍ ግን ያልተጠበቀውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ አድርጓቸዋል።
ከዚህም ባሻገር በኢራን ያለውን የኢንተርኔት ገደብ እንደሚያላሉና ፖሊሶች ጸጉራቸውን የማይሸፍኑ ሴቶች ላይ የሚወስደውን ያልተገባ እርምጃ እንደሚቃወሙ መናገራቸውም የመራጮችን ድምጽ እንዲያገኙ ሳያግዛቸው አልቀረም።
በኢራን በምርጫ መሳተፍ ከሚችለው 61 ሚሊየን ህዝብ በአሁኑ ምርጫ የተሳተፈው 40 በመቶው ብቻ ነው።
ይህም ከ1979ኙ አቢዮት ወዲህ ዝቅተኛው የመራጭ ቁጥር የተመዘገበበት ነው የተባለ ሲሆን፥ ኢራናውያን በምዕራባውያን ማዕቀብ በተዳከመው ኢኮኖሚ እና በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ቁጣቸውን ለመግለጽ ድምጻቸውን ከመስጠት ተቆጥበው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪው አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ግን የመራጮቹ ቁጥር ከተጠበቀው በታች ቢሆንም “ስርአቱ ላይ ተቃውሞን ማሳያ አይደለም” ብለዋል።