ፔዚሺኪያን በመጀመሪያው ዙር ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ስላልቻሉ በመጭው ሐምሌ አምስት በሚካሄደው ምርጫ ይወዳደራሉ
በኢራኑ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለዘብተኛ የተባሉት ዕጩ ማን ናቸው?
በወግ አጥባቂዎች በተሞላው የኢራን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ፣ የሴቶችን መብት እና የበለጠ ማህበራዊ ነጻነትን የሚደግፉት እና ከምዕራባውያን ጋር ጥንቃቄ የተሞላበት ግንኙነት እንዲኖር የሚፈልጉት ለዘብተኛው እጩ ማሱድ ፔዚሺኪያን ይባላሉ።
ፔዚሺኪያን ባለፈው ረቡዕ እለት በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ወግ አጥባቂውን ሰኢድ ጃሊሊን በጠባብ ውጤት ያሸነፉ ቢሆንም፣ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ስላልቻሉ በመጭው ሐምሌ አምስት በሚካሄደው ምርጫ ይወዳደራሉ።
የቀድሞው የጤና ሚኒስትር የሆኑት 69 አመቱ የህክምና ዶክተር ፔዚሺኪያን የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒን ጠንካራ ጸረ-ምዕራባውያን አቋም የሚያንጸባርቁትን እጩዎች በመብለጥ ነው ወደፊት የመጡት።
አርብ እለት በተካሄደው ምርጫ በጠባብ ውጤት ያሸነፉት ፔዚሺኪያን፣ በሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ የሞቱን ኢብራሂም ራይሲን ለመተካት በሚደረገው ምርጫ ይሳተፋሉ። የፔዚሺኪያን የማሸነፍ እድል በምርጫ ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ባጠናቀቀው የአሁኑ ወደግአጥባቂ የፓርላማ አፈጉባኤ ባቀር ቋሊባፍ ደጋፊዎች ላይ የተንጠለጠለ ነው።
ፔዚሽኪያን ለውጥን ቢያቀነቅኑም፣ ለኢራን የጸጥታ አወቃወር እና ሃይማኖታዊ ህጎችን ተአማኝ እንደሆኑ ይገለጻል። የፔዚሺኪያን እይታ በሴቶች አለባበስ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ ከነበሩት የካማኒ ቀኝ አጅ ራይሲ ጋር በንጽጽር እየቀረበ ይገኛል።
የፔዚሺኪያን የምርጫ ዘመቻ ከፍ ወደአለ ደረጃ ላይ የደረሰው በቀድሞው ፕሬዝደንት ሞሀመድ ካታሚ የሚመሩት የለውጥ አቀንቃኞች ድጋፍ ከሰጧቸው በኋላ ነው።
ፔዚሺኪያን ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነ የኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዳይመለስ ለሚፈልጉት ወግአጥባቂዎች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።ነገርግን በኢራን ሀይማኖታዊ እና ሪፐብሊካን ስርአት መሰረት የውጭ እና የኑክሌር ጉዳዮችን ጨምሮ በቁልፍ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያሳልፉት ካሚኒ ናቸው። በዘህ ምክንያት በርካታ መራጮች ፔዚሺኪያን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል ስለመፈጸማቸው ይጠራጠራሉ።
በፈረንጆቹ 2018 የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኑክሌር ስምምነት "ለአንድ ወገን ያዳላ እና በፍጹም ሊፈረም የማይገባው ነው" በማለት በኢራን ላይ በድጋሚ ማዕቀብ ጥለዋል።
ይህ የትራምፕ እርምጃ ቴህራን ቀስበቀስ ስምምነቱን እንድትጥስ አድርጎለታል።
በ2015 በተደረሰው ጆይን ኮምፕሪሄንሲቭ ፕላን ኦፍ አክሽን (ጄሲፒኦእ) ወይም በኢራን ኑክሌር ስምምነት መሰረት፣ ኢራን በቀጣይ 15 አመታት ውስጥ የምታበለጽገው ዩራኒየም ከ3.67 በመቶ እንዳታስበልጥ እና የዩራኒየም ክምችቷን እንድትቀንስ ተስማምታለች።