የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በፈጣን የሰላም ስምምነት አልያም በኑክሌር በፍጥነት ሊቋጭ እንደሚችል ተገለጸ
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአጭር ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ እንደ አብነት ተወስዷል
ኔቶ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መስጠቱን ካቆመ ጦርነቱ በፍጥነት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በፈጣን የሰላም ስምምነት አልያም በኑክሌር ሊቋጭ እንደሚችል ተገለጸ።
ለአንድ ሳምንት በኒል በልዩ ዘመቻ መልኩ የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት 17ኛ ወሩን ይዟል።
ይህ ጦርነት በየጊዜው የማይገመቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያስመዘገበ ሲሆን ምዕራባዊያን እና የኔቶ አባል ሀገራት የጦር መሳሪያ ለዩክሬን በመስጠት ላይ ናቸው።
የሩሲያ ጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሀላፊ ድሚትሪ ሜድቮዴቭ ለታስ በሰጡት መግለጫ የዩክሬን ጦርነት በፈጣን የሰላም ስምምነት አልያም በኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊቋጭ ይችላል ብለዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ በጃፓን ሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ላይ ቦምብ ከጣለች በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፍጻሜውን እንዳገኘ ሜድቬዴቭ ተናግረዋል።
ይህ ጦርነት ለ300 ሺህ ዜጎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል የተባለ ሲሆን የዩክሬን ጦርነትም ወደዛው እያመራ መሆኑ ተጠቁሟል።
ሜድቬዴቭ አክለውም ኔቶ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መስጠቱን ቢያቆም የዪክሬን መሰረተ ልማቶች ከውድመት ማዳን ይቻላልም ብለዋል።
ነገር ግን ኔቶም ዩክሬንን መርዳቱን ከቀጠለ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ውጊያ ሊነሳ እንደሚችል ሜድቬዴቭ አስጠንቅቀዋል።
17ኛ ወሩ ላይ እሚገኘው ይህ ጦርነት አንድም በፍጥነት በሚፈጸም የሰላም ስምምነት አልያም በኑክሌር ጦርነት ይጠናቀቃል ተብሏል።
ከምዕራባዊያን በእርዳታ ያገኘቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በመያዝ መልሶ ማጥቃት መጀመሯን የገለጸችው ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻው ለጊዜው መቋረጡን በመናገር ላይ ነች።
ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ አስቀድሞ መክሸፉን ገልጻ በባክሙት አቅራቢያ ያለውን የዩክሬን ወታደሮች በመክበብ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጓን አስታውቃለች።