ሶስት ሀገራት ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትቆጠብ ጠየቁ
ኢራን እና አጋሮቿ "በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የመፍጠር አጋጣሚን የሚያሰናክል እርምጃ ከፈጸሙ ኃላፊነት ይወስዳሉ"ብሏል መግለጫው
አሜሪካ በቀጣናው ውጥረት መጨመሩን ተከትሎ ተጨማሪ የጦር መርከቦች ወደ መካከለኛ ምስራቅ ማሰማሯቷን ይፋ አድርጋለች
ሶስት ሀገራት ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትቆጠብ ጠየቁ።
ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪይግደም (ዩክ) ኢራን እና አጋሮቿ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገራቱ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢራን እና አጋሮቿ ቀጣናዊ ውጥረቱን ከሚያባብስ እና የተኩስ አቁም ጥረቶችን ከሚያደናቅፉ ጥቃቶች እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
መግለጫው የወጣው በእስራኤል እና በኢራን እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ መካከል ያለው ውጥረት ማየሉን ተከትሎ ነው።
ኢራን እና አጋሮቿ "በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የመፍጠር አጋጣሚን የሚያሰናክል እርምጃ ከፈጸሙ ኃላፊነት ይወስዳሉ"ብሏል መግለጫው።
ሀገራት "ኳታር፣ግብጽ እና አሜሪካ ተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ጥረት" በበጎ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል። እኝህ ሀገራት የኳታሩ ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አል ታኒ፣ የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ እና አሜሪካ አስቸኳይ ድርድር እንዲጀመር ያቀረቡን ጥሪም ደግፍውታል።
የእስራኤል ደህንነት ኢራን በቀናት ውስጥ እስራኤልን ልታጠቃ እንደምትችል ገልጿል። ጥቃቱ የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ከመጀመሩ ከሀሙስ በፊት ሊቃጣ እንደሚችል እና በእስራኤል እና በኢራን መካከል በሚደረጉ ንግግሮች አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል።
በቅርቡ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን እና የሄዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር በቤሩት ከተማ ዳርቻ ተገድለዋል።
ኢራን እና ሀማስ ለግድያ ተጠያቂ ያደረጓትን እስራኤልን እንደሚበቀሉ ዝተዋል።
ሹክርን መግደሏን ወዲያውኑ ይፋ ያደረገችው እስራኤል፣ የሀኒየህን ግድያ ቆይታ ነው ያመነችው።
አሜሪካ በቀጣናው ውጥረት መጨመሩን ተከትሎ ተጨማሪ የጦር መርከቦች ወደ መካከለኛ ምስራቅ ማሰማሯቷን ይፋ አድርጋለች።