እስራኤል ከኢራን ይሰነዘራል ተብሎ ለሚጠበቀው ጥቃት ምን አይነት ዝግጅት እያደረገች ነው?
ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ደም እንዲከማችና ተቀጣጣይ የፋብሪካ ኬሚካሎች በመሬት ውስጥ እንዲቀበሩ አዛለች
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመከላከልም ለማጥቃትም ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል
በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እያየለ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ እስራኤል ዜጎቿን ለመጠበቅ እና የጉዳት መጠኖችን ለመቀነስ መጠነ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት የሀማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒየህ በቴሄራን መገደሉን ተከትሎ ከፍተኛ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ የዛተችውን ኢራን ጥቃት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡
በወታደራዊው መስክ ጥቃቶቹን ለመመከት እና የጉዳት መጠናቸውን ለመቀነስ ከሚደረገው ሁለገብ ዝግጅት ባለፈ ቴልአቪቭ ዜጎቿን እና መሰረተ ልማቶቿን ለመጠበቅ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደምትገኝ ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ከእነዚህ መካከል ሆስፒታሎች እና አምቡላንሶች በቂ የደም ክምችት እንዲኖራቸው ማስቻል አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው ደም በመሬት ውስጥ በተዘጋጁ ማዕከላት እንዲከማች አድርጋለች፡፡
ይህም በጤና ተቋማቶቿ ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ እጥረት እንዳይከሰት ለማስቻል ሲሆን የምድር ውስጥ ሆስፒታሎች በጥቃቱ ሊጎዱ የሚችሉ ተጎጂዎችን ለማከም በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንዲገኙ ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ጥቃቶች በሚሰነዘሩ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ የተገጠሙ የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሚያሰሙ ሳይረኖች ጥገና እና የመስራት አቅማቸው እየተሸሻለ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም የጥቃት ኢላማ ናቸው ተብለው በተለዩ ስፍራዎች ላይ ጥቃት በሚሰነዘር ጊዜ ዜጎች ራሳቸውን ከጉዳት እንዲጠብቁ የጽሁፍ መልዕክት በእጅ ስልኮቻቸው ላይ እንዲደርሳቸው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የሀገሪቱ ዜጎች በክፍት ቦታዎች ላይ መሰባሰቦችን እንዲያቆሙ እንዲሁም ሁኔታዎችንም በንቃት እንዲከታተሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተላልፎላቸዋል፡፡
በፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ ተቀጣጣይ ኬሚካሎች የጉዳት መጠኖችን ሊያባብሱ ስለሚችሉ ኢላማ ከተደረጉ ስፍራዎች እንዲርቁ እና በመሬት ወስጥ እንዲቀበሩም ተደርጓል፡፡
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሂዝቦላህ የሮኬት ኢላማ ክልል ውስጥ ወጥተው በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም የሂዝቦላህ ሮኬቶች የደንበር አካባቢን ተሻግረው በትላልቅ ከተሞች ማዕከላዊ ስፍራዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚያስችል አቅምን አዳብረዋል፡፡
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለተለያዩ አገልግሎቶቿ እና ተቋሞቿ ከጥቃት የሚጠበቁበትን አማራጭ መንገዶችን ስታመቻች የሰነበተችው እስራኤል ባለፉት 10 ቀናት የኢራንን የአጸፋ ምላሽ ፍራቻ የምታደርጋቸው ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናክረዋል፡፡
በትላንትናው እለት ከአዳዲስ ምልምል ወታደሮች ጋር ቆይታ ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመከላከልም ለማጥቃትም ዝግጅት እያደረግን ነው፤ በተመሳሳይ ሰአት ጉዳቶችን ለመቀነስ እያደረገነው ያለው ቅድመ ዝግጅት ቀጥሏል ብለዋል፡፡
አስራኤል በአሁኑ ወቅት ራሷን በተለያዩ አቅጣጫዎች በጦርነት ስጋት ውስጥ ተከባ አግኝታዋለች፡፡ የሊባኖሱ ሂዝቦላህ ፣ የየመኑ ሀውቲ እና ከኢራን ጋር በጋዛው ጦርነት ምክንያት የገባችበት መካረር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡
የእስማኤል ሀኒየህን ግድያ ተከትሎ ከኢራን ሊሰነዘር የሚችለው የአጸፋ ምላሽ ምን አይነት ሊሆን እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም፡፡
ሂዝቦላህ በበኩሉ በተናጠል እና ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር መጠነ ሰፊ ጥቃት በእስራኤል ላይ እንደሚፈጽም ዝቷል፡፡