ቴህራን በደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ከዛተች ከቀናት በኋላ ነበር መርከቧ የተያዘችው
ኢራን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት በሚል የያዘቻትን መርከብ ሰራተኞች መልቀቋን ገልጻልች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን የፖርቹጋል ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ የነበረችው እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላት መርከብ ሰራተኞች ተለቀዋል፤ መርከቧ ግን እንደተያዘች ትቆያለች ብለዋል።
ቴህራን በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ከዛተች ከቀናት በኋላ ነበር የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ 25 ሰራተኞች ያሏትን መርከብ በፈረንጆቹ ሚያዝያ 13 በሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ የያዘው።
ኢራን ይህን ወሳኝ የባህር መተላለፊያ እንደምትዘጋውም አስፈራርታ ነበር።
አሚርአብዶላሂያን "የተያዘችው መርከብ ራዳሯን ወደ ኢራን የባህር ክልል በማዞር የማሪታይም ህግን ስለጣሰች በህግ ቁጥጥር ስር ትቆያለች" ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በትናንትናው እለት በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
የሰራተኞቹ መለቀቅ ሰብአዊነትን እንደሚያሳይ የገለጹት ሚኒስትሩ ከመርከቧ ካፒቴን ጋር ወደ ሀገራቸው ይሸኛሉ ብለዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል ኤምኤስ አይረስ የተባለችው ይህች መርከብ የተያዘችው "የማሪታይም ህግ" በመጣሷ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት እንዳላት በመረጋገጡ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ኤምኤስሲ መርከቧን የተከራያት በከፊል የእስራኤል ባለሀብት ኢያል ኦፈር ንብረት ከሆነው ዞዲያክ ማሪታይም ጋር በሽርክና ከሚሰራው ጎርታል ሸፒንግ ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ጸረ- እስራኤል የሆኑ ታጣቂዎች በመደገፍ ክስ የሚቀርብባት ኢራን የሶሪያውን ጥቃት ለመበቀል ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ቀጥተኛ የሚሳይል እና ድሮን ጥቃት ሰንዝራለች።
ይህን ተከትሎ እስራእልም በኢራን ላይ የበቀል ጥቃት አድርሳለች የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ኢራን ውስጥ በእስራኤል ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት ሰርጎገቦች ያደረሱት ነው ስትል ኢራን አቃላዋለች።
የኢራን ምላሽ በቀጣናው ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚለውን ስጋት ቀንሶታል።
ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነታቸውን ያሳዩት በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ታጣቂዎች በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ባለፉት ሳምታት ጨምሯል።