ኢራን በአሜሪካ ለተገደለባት የጦር መሪ 50 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት ጠየቀች
ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ ከአራት ዓመት በፊት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ኢራቅ ውስጥ መገደሉ ይታወሳል
ኢራን ብሔራዊ ጀግናዬን እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል በሚል ዶናልድ ትራምፕ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠይቃለች
ኢራን በአሜሪካ ለተገደለባት የጦር መሪ 50 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት ጠየቀች።
በኢራናዊያን ተወዳጅ እንደሆኑ የሚነገረው ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ ከአራት ዓመት በፊት በኢራቅ መዲና ባግዳድ መገደላቸው ይታወሳል።
የኢራን እስላማዊ አብዮት ጦር መሪ የነበሩት ጀነራል ቃሲም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በተሰነዘረባቸው የድሮን ጥቃት ተገድለዋል ተብሏል።
ጀነራሉ በአሜሪካ የተገደሉት ዋሸንግተን በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያላትን ጥቅም እንድታጣ የተለያዩ ጥቃቶችን መርተዋል በሚል ነው።
የኢራን ብሔራዊ ጀግና ናቸው የተባሉት የ62 ዓመቱ ጀነራል ቃሲምን ደም ለመክፈል ቴህራን የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን አሁን ደግሞ አሜሪካ 50 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንድትከፍላት መጠየቋን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት ባስተላለፈው ትዕዛዝ በግድያው የተሳተፉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ 42 ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከልም የቀድሞው የአሜቲካ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ መከላከያ ሚንስትሩ ማርክ ኢስፔር እና ሌሎችም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ጀነራል ሱሌማኒ ከፈረንጆቹ 1980 እስከ 1988 በተካሄደው የኢራን-ኢራቅ ጦርነትን በመምራት እና ድል በማስመዝገባቸው በሀገሪቱ እንደ ብሔራዊ ጀግና ይታያሉ።
አሜሪካ የቀድሞ ባለስልጣናቷ ለኢራን ተላልፈው እንዲሰጡ እና ስለቀረበላት የካሳ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።