በዮርዳኖስ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 3 የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ ከ34 በላይ ቆሰሉ
የድሮን ጥቃቱ “በኢራን በሚደገፉ አክራሪ ቡድኖች” ተፈጽሟል ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፥ አጻፋዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ዝተዋል
ኢራን ውንጀላው “በቀጠናው ያለውን እውነታ ለመሸፋፈን ያለመ ነው” በሚል ውድቅ አድርጋዋለች
ዮርዳኖስን ከሶሪያ በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ተገደሉ።
በጥቃቱ በጥቂቱ 34 ወታደሮች መቁሰላቸውንም ነው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተናገሩት።
በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት በሶሪያ እና ኢራቅ የሚንቀሳቀሱ “በኢራን የሚደገፉ አክራሪ ቡድኖች” ተጠያቂ መሆናቸውንም ባይደን ገልጸዋል።
የድሮን ጥቃቱን የትኛው ቡድን እንደፈጸመው ለማወቅ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን በመጥቀስም ዋሽንግተን ፈጣን የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝተዋል።
በኢራቅ የሚንቀሳቀሰው “ኢስላሚክ ሬዚስታንስ” በዮርዳኖስና ሶሪያ ድንበር ለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ማለቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢራን በበኩሏ በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ ከተፈጸመው የድሮን ጥቃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።
የአሜሪካ ክስ “በቀጠናው ያለውን እውነት ለማድበስበስ ያለመና ልዩ ፖለቲካዊ ግብ ያለው ነው” ብለዋል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ።
ዋሽንግተን ከሶሪያ እስከ ኢራቅና የመን ድረስ በመዝለቅ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች ቀጠናውን እያተራመሰ መሆኑን ቴህራን ደጋግማ ገልጻለች።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በሶሪያ እና ኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ከ150 በላይ የጥቃት ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፥ በጥቂቱ 70 ወታደሮች መቁሰላቸው ተገልጿል።
የሶስት ወታደሮች ህይወት ያለፈበትና ከ34 በላይ የቆሰሉበት ጥቃትም ከባድ ጉዳት በማድረስ ቀዳሚው ሆኗል።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ሀይሎች አሜሪካ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እጇን ማስገባቷን እንድታቆም ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የዮርዳኖሱ ጥቃት የዋሽንግተንን አጻፋዊ እርምጃ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሚገኙት ዴሞክራቱ ባይደን በኢራን እና በምትደግፋቸው ታጣቂዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃ ቀጣይ እጣፈንታቸውን ይወስናል የሚሉ አስተያየቶችም ከሀገሪቱ ፖለቲከኞች እየተነሳ ነው።
ይህም የጋዛው ጦርነት ይበልጥ አድማሱን በማስፋት የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን ውጥረት ያባብሰዋል ተብሏል።