የኢራኑ ፕሬዝዳንት በጥቃት መገደላቸው የሚያሳይ መረጃ አለማግኘቱን የሀገሪቱ ጦር ገለጸ
ፕሬዝዳንቱን የጫነችው ሂልኮፕተር ካረፈች በኋላ በእሳት መያያዟን የኢራን ጦር አስታውቋል
ባሳለፍነው እሁድ በደረሰው በዚህ አደጋ የኢራንን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት በጥቃት መገደላቸው የሚያሳይ መረጃ አለማግኘቱን የሀገሪቱ ጦር ገለጸ፡፡
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬይሲ ባሳለፍነው እሁድ ከአዘርባጃን በምትዋሰነው የኢራን የድንበር ከተማ ግድብ መርቀው ሲመለሱ የተሳፈሩበት ሄሊኮፕተር አደጋ አጋጥሞት በድምሩ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
በከባድ አየር ንብረት ምክንያት ተከስቷል የተባለው ይህ አደጋ ፕሬዝዳንቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚራብዶላሂያንን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
የኢራን ጦር በሂልኮፕተር አደጋው ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡
ለፕሬዝዳንቱ እና ሌሎች ባለስልጣናት ህይወት ማለፍ ምክንያት ነው የተባለው ይህ አደጋ በተሰነዘረበት ጥቃት መድረሱን የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ አለማግኘቱ ተገልጿል፡፡
ኢራን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መቼና እንዴት ታካሂዳለች?
እንደ ምርመራው ሪፖርት ከሆነ ፕሬዝዳንቱ የተሳፈሩባት ሂልኮፕተር በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ላይ ካረፈች በኋላ በእሳት ተያይዛ ተሳፋሪዎቹም ህይወታቸው በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ምርመራው ይቀጥላል የተባለ ሲሆን ተጨማሪ የምርመራ ውጤቶች በቀጣይ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም የሀገሪቱ ጦር አስታውቋል፡፡
በኢራን ህገ መንግስት መሰረት አሁን ላይ የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞሀመድ ሞክበር ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡
የ68 ዓመቱ ሞሀመድ ሞክበር የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ካሚኒ የቅርብ ሰው ናቸው የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ የፊታችን ሐምሌ ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ አስታውቃለች፡፡