የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ መሸሸጋቸው ተሰማ
እስራኤል የሄዝቦላህን ዋና አዛዥን መገድሏን ተከትሎ ነው ሀይማኖታዊ መሪው ወደ ሌላ ስፍራ የተዛወሩት
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር በትናንቱ የተመድ ንግግራቸው የእስራኤል ረጅም ክንድ በተሄራን የማይደርስበት ስፍራ የለም ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ስፍራ መዘዋወራቸው ተነግሯል፡፡
የሄዝቦላ ዋና አዛዥ ሀሰን ነስረላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ተከትሎ የመካከለኛው ምስራቅ ዛሬ ላይ የሚገኝበት ውጥረት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጨምሯል፡፡
የመሪውን ሰይድ ሀሰን ናስራላህ መገደል ያረጋገጠው ሄዝቦላህ በመግለጫው ጋዛን እና ፍልስጤምን በመደገፍ እንዲሁም የሊባኖስን የተከበረ ህዝብ ለመከላከል ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን ውጊያ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሮይተርስ ከኢራን የውስጥ ምንጮች አገኝሁ ብሎ ባሰራጨው መረጃ ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታዎችን ተከትሎ ካሚኒ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ሚስጥራዊ ስፍራ ተጓጉዘዋል፡፡
በተጨማሪም የኢራን አስተዳደር ከሄዝቦላ መሪዎች እና በአካባቢው ከሚገኙ ቴሄራን ድጋፍ ከምታደርግላቸው ታጣቂ ቡድኖች ጋር ስለ ቀጣይ እርምጃዎች አየተመካከረ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በተመድ 79ኛው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “ቴሄራን ለሚገኙ አምባገነኖች መልዕክት አለኝ፤ ጥቃት የምትፈጽሙ ከሆነ ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን። የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት የኢራን ክፍል የለም፤ ይህ የመካከለኛው ምስራቅ እውነት ነው” ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ካሚኒ ሙስሊሞች በጋራ ተነስታችሁ እስራኤልን ተጋፈጡ ሲሉ ጥሪ አስተላፈዋል፡፡
የቀጠናው ሁለንተናዊ ሁኔታ በሄዝቦላህ ጥንካሬ ላይ ይወሰናል ያሉት ካሚኒ ሙስሊሞች በየትኛውም ሁኔታ ከሄዝቦላህ ጎን ቆመው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ሀማስ በበኩሉ የሀሰን ነስራልህ ግድያ የማደርገውን የትግል እንቅስቃሴ የሚያበረታ እንጂ የሚያዳክም አይደለም ብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈ እስራኤል የኢራን አውሮፕላኖች በሊባኖስ የአየር ክልል የሚታዩ ከሆነ በቤሩት አየር ማረፍያ ጥቃት እንደምትሰነዝር ማስጠንቀቋን ተከትሎ ሊባኖስ የኢራን አውሮፕላን በቤሩት እንዳያርፉ ከልክላለች፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሀይል ቃል አቀባይ ሬር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ የእስራኤል አየር ሀይል የሊባኖስን የአየር ክልል በንቃት እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢራን ለሄዝቦላ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገች እንደምትገኝ መረጃ እንደደረሳቸው የተናገሩት ቃል አቀባዩ “ይህ እንዲሆን አንፈቅድም፤ ለማንኛውንም ጠብ አጫሪ ድርጊት ምላሻችን ፈጣን ነው” ብለዋል፡፡
ሄዝቦላህ የመሪውን መገደል ተከትሎ ምንም እንኳን ያደረሱት ጉዳት አነስተኛ ቢሆንም በዛሬው እለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬት እና ሚሳኤሎችን ወደ ቴልአቪቭ አስወንጭፏል፡፡