እስራኤል ከዋነኛ አጋሯ አሜሪካ በሊባኖስ ተኩስ እንድታቆም የቀረበላትን ጥሪ ውድቅ አደረገች
ቴል አቪቭ በሊባኖስ የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች
አሜሪካ እና አጋሮቿ እስራኤልና ሄዝቦላህ ለ21 ቀናት ተኩስ እንዲያቆሙ በይፋ መጠየቃቸው ይታወሳል
እስራኤል በሊባኖስ የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ እንደምትቀጥል አስታወቀች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በሰሜን (ሊባኖስ) ምንም አይነት የተኩስ አቁም አይኖርም” ብለዋል።
“አሸባሪውን የሄዝቦላህ ላይ ቡድን በጠንካራ ሃይላችን አሸንፈን የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ወደቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ ውጊያው ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።
የሚኒስትሩ አስተያየት ከእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት የቀረበውን የ21 ቀናት የተኩስ አቁም ጥያቄ ውድቅ ያደረገ ነው።
በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ለማድረግ ወደ አሜሪካ የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ሆኑ መከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት የሊባኖሱ ጥቃት ዋነኛ አላማ በሰሜናዊ እስራኤል በሄዝቦላህ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ መሆኑን ሲናገሩ ሰንብተዋል።
በእስራኤል የአየር ድብደባ በሶስት ቀናት ውስጥ ከ500 በላይ ዜጎቿ የተገደሉባት ሊባኖስ በአሜሪካ እና አጋሮቿ የቀረበውን የ21 ቀናት የተኩስ አቁም ጥሪ መቀበሏን ማስታወቋን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ማካቲ በሊባኖስ እና ሄዝቦላህ መካከል በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የፈረንሳይ እና የብሪታንያን ጨምሮ የተለያዩ የአለም ሀገራት መሪዎችም ተኩስ አቁም አይኖርም ያለችውን እስራኤል በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጥረቱን እንድታረግብ እየጠየቁ ነው።
ቴል አቪቭ ከ18 አመት በኋላ ወደ ሊባኖስ የምድር ጦሯን ልታስገባ እንደምትችል መግለጿም ግጭቱ ወደለየለት ጦርነት አምርቶ ቀጠናዊ መልክ ሊይዝ ይችላል የሚለውን ስጋት አንሮታል።
ለሄዝቦላህ ወታደራዊና የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች የምትባለው ኢራንም በሃይማኖታዊ መሪዋ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በኩል ሄዝቦላህን በማሞገስ ዋሽንግተንን ወቅሳለች።
የባይደን አስተዳደር ከህዳሩ ወር ምርጫ በፊት የቴል አቪቭን የሊባኖስ ድል ይሻል ያሉት ሃሚኒ፥ ቴህራን እስራኤልና ሄዝቦላህ ወደ ጦርነት ከገቡ ምን አይነት እርምጃ እንደምትወስድ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ይሁን እንጂ 40 ሺህ የሚጠጉ በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የየመን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ታጣቂዎች ከሄዝቦላህ ጎን ለመሰለፍ ወደ ሊባኖስ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸው በትናንትናው እለት መገለጹ የሚታወስ ነው።