ኢራን የአሜሪካን የድጋፍ ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ድጋፉ ስርጭቱን ይበልጥ ለማባባስ ምናልባትም ደግሞ እንዳይጠፋ ለማድረግ ቢሆንስ በሚልም ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ
“አሜሪካ የኢራን ቁጥር አንድ ጠላት ነች”-አያቶላህ አሊኻሚኔይ
ኢራን የአሜሪካን የድጋፍ ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ኃይማኖታዊው መሪ እና የአብዮቱ የበላይ ጠባቂ አያቶላህ አሊ ኻሚኔይ ኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ አሜሪካ ድጋፍ ላድርግ ማለቷን ውድቅ አድርገዋል፡፡
በሃገራቸው በመከበር ላይ ያለውን አዲስ ዓመት አስመልክተው በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር “አሜሪካ የኢራን ቁጥር አንድ ጠላት ነች” ብለዋል፡፡
“ራሷ ተቸግራ እያለ እንዴት ልትረዳን ትችላለች” በሚል ባደረጉት ስላቅ አዘል ንግግርም ቫይረሱን ሳትፈጥረው አልቀረም በሚል የሚከሷት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
“የተረገመች ተንኮለኛ” ያሏት አሜሪካ መሪዎቿ “ሽብርተኛና ውሸታም” መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኃይማኖታዊ መሪው አሜሪካ ላድርግ የምትለው ድጋፍ የወረርሽኙን ስርጭት ይበልጥ ለማባባስ ምናልባትም ደግሞ እንዳይጠፋ ለማድረግ ቢሆንስ በሚልም ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ ፡፡
ኻሚኔይ “እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን የኮራና ወረርሽኝን ጨምሮ የትኛውንም አደጋ የመቋቋም አቅም አላት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚድልኢስት ሞኒተር ዘገባ ኻሚኔይ ቫይረሱ ወደ ሃገሪቱ መግባቱ ከተረጋገጠበት ከየካቲት 10 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ 1 ሺ 685 ኢራናውያን መሞታቸውንና 22 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያቸው መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡