የሱዳን መንግስት በአሜሪካ መንግስት በቀረበው የድርድር ጥያቄ መሰረት ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ጋር ለመደራደር ተስማማ
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ባወጣው መግለጫ ጦሩ ለመደራደር ፈቃደኛ ቢሆንም ቅድመ ሆኔታዎችን ግን አስቀምጧል
15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት 10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዲፈናቁሉ እና 10ሺ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል
ሱዳን ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ጋር ለመደራደር ተስማማች
በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረብያ መሪነት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንዲካሄድ ለቀረበው የድርድር ጥሪ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መንግስት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል።
የሱዳን መንግስት ለመነጋገር ፍቃጀኛ የሆነው በሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ ነው።
አሜሪካ የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በፈረንጆቹ ነሐሴ 14 በስዊዘርላንድ የተኩስ አቁም ንግግር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ፤
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ "በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሰብአዊ እርዳታ ለተቸገሩ ሁሉ እንዲደርስ" በንግግሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ወዲያው ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
በገብጽ ፣ በጂቡቲ ፣ በኬንያ ፣ በሳኡዲ አረብያ እና በሌሎች አካላት ሁለቱን ተፋላሚዎች ለማደራደር የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ሳይሆን ዘልቋል፡፡
የሀገሪቱ ጦር በሀገር ከጂነት ከፈረጀው የፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ለመደራደር ፈቃደኝነት አላሳየም፡፡ የጄኔቫው ጉባኤ ሁለቱን አካላት በእንድ ክፍል ውስጥ ለማገናኝት ለወራት ከተሞከሩ ሙከራዎች ቀዳሚው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ቢልም፤ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ጦር ከተቆጣጠራቸው ስፍራዎች እንዲለቅ እና ሌሎች አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ውግያ እንዲያቆም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም በድርድሩ አጀንዳዎች ዙርያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች ስምንቱን መቆጣጠር የቻለው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎ የሀገሪቱ ጦር ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ የመቀበል እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ያሳዩት ፈቃደኝነት አንድ እርምጃ ነው ብሏል፡፡
በጄኔቫ የሚካሄደው ድርድር በአሜሪካ እና ሳኡዲ መሪነት የሚደረግ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብኤሜሬትስ በታዛቢነት እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡
15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት 10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዲፈናቁሉ እና 10ሺ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች የተስፋፉ ሲሆን በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በምዕራብ ዳርፉር የብሔር ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ ይቀርብበታል።
አሜሪካ በቅርቡ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድሜዳሜ ላይ መድረሷን ማሳወቋ ይታወሳል።