በዘንድሮው ምርጫ በትራምፕ እና ሃሪስ መካከል በሚደረገው ፉክክር ያስቀመጡት አሸናፊ ያልተጠበቀ ሆኗል
የነጩን ቤተ መንግስት ቁልፍ ማን ሊረከብ ይችላል?
ከአሜሪካ ተሻግሮ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተጽእኖ ያለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ህዳር 5 ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡
በበርካታ ድራማዊ እና አወዛጋቢ ሁነቶች የታጀበው የዘንድሮው ምርጫ የእጩዎች እና ሁኔታዎች መቀያየር አሸናፊውን ለመገመት አዳጋች አድርጓል፡፡
አሜሪካዊው የታሪክ ምሁር አለን ሊችማን ከ1984 ጀምሮ ለ40 አመታት በተካሄዱ ምርጫዎች ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ማን እንደሚሆን ባስቀመጧቸው ትንበያዎች ተሳስተው አያውቁም፡፡
የታሪክ ምሁሩ የነጩ ቤት ቁልፎች በተሰኝው የትንበያ ቀመራቸው የእጩዎችን ወቅታዊ አቋም እና አጠቃላይ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ሂደት በመገምገም ነው ትንበያዎችን የሚያስቀምጡት፡፡
13 ወሳኝ ጥያቄዎች በትንበያ ቀመራቸው ውስጥ ያካተቱ ሲሆን የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ደግሞ አሸናፊውን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ እንደሆኑ ይናገራሉ
ከእነዚህ ጥያቄዎች በስድስት እና ከእዚያ በላይ ጥያቄዎች ተፈትኖ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኝ እጩ አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ከጥያቄዎቹ መካከል የረጂም እና የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ፣ ወቅታዊ የፓርቲ አቋም እና ተቀባይነት ፣ ህዝባዊ አመጽ ፣ የፖሊሲ ፈተናዎች ፣ የውጭ ጉዳይ እና ወታደራዊ ስኬቶች ፣ የእጩው ተወዳጅነት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በምርጫ ውድድሩ መጀመሪያ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙት ዴሞክራቶች የተሻለ አድል እንደነበራቸው የሚያመላክቱ ነጥቦች ነበሩ፤ ከእዚያ በኋላ የተፈጠሩ አዳዲስ ጉዳዮች ግን የምርጫውን አሸነፊ እንደከዚህ ቀደሙ በእርግጠኛነት ለመናገር አያስደፍሩም ሆኖም የታሪክ ምሁሩ የተንበያ ሂደታቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው ጆ ባይደንን ተክተው የዴሞክራት እጩ እንደሚሆኑ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በአለን ሊችማን የመመዘኛ ጥያቄዎች ስድስቱን ማለፍ ችለዋል፡፡
ሃሪስ በተለይ ከግል ጉዳይ ጋር የሚገናኝ የቅሌት ዜናዎች ስለሌለባቸው ፣ እንዲሁም በሴቶች እና በጥቁሮች ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው ተቀባይነት እና በሌሎችም በስድስት ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ጥሩ አፈጻጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
የዶናልድ ትራምፕን ውጤት ይፋ ያላደረጉት የታሪክ ምሁሩ አሁን ባለው ሁኔታ ሃሪስ የተሻለ እድል እንዳላቸው ፍንጭ ቢሰጡም ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ባሉት ቀናት የሚኖሩ ለውጦች አሸናፊውን ለመተንበይ ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡
የመጨረሻ የትንበያ ውጤታቸውን ካማላ ሃሪስ በይፋ የዴሞክራት እጩ ከሚደረጉበት የነሀሴ 19ኙ የዴሞክራቶች ጉባኤ በኋላ በይፋ እንደሚገልጹ ተናግረዋል፡፡