ኢራን 2025 ለኑክሌር ጉዳይ "ወሳኝ አመት" ነው አለች
የኢራን መሪዎች ዋና ስጋት ትራምፕ እስራኤል የኢራንን የኑክሌር ጣቢያዎች እንድትመታ ያበረታቷታል የሚል ነው
ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በ2015 ኢራን ዩራኒየም ማበልጸጓን እንድትገታ ያደረጉትን ስምምነት በ 2018 ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሚያደርጉት ጫና እየተዘጋጀች ያለችው ኢራን 2025 ለኑክሌር ጉዳይ ወሳኝ አመት መሆኑን በትናንትናው እለት ገልጻለች።
ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በ2015 ኢራን ዩራኒየም ማበልጸጓን እንድትገታ ያደረጉትን ስምምነት በ 2018 ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት የሚያስችለውን ዩራኒየም ማበልጸጓን ለመግታት የተስማማችው፣ አሜሪካ እና ተመድ በምላሹ የጣሉትን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲያላሉላት ነበር።
ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው በሚል ነበር ጥያቄ ያነሱት።
"የኢራንን የኑክሌር ጉዳይ በሚመለከት 2025 ወሳኝ አመት ይሆናል" ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አራቅቺ በቤጂንግ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።ነገርግን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም አመቱ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢራን መሪዎች ዋና ስጋት ትራምፕ እስራኤል የኢራንን የኑክሌር ጣቢያዎች እንድትመታ ያበረታቷታል የሚል ነው።በመጭው ጥር 20፣2024 ትራምፕ ወደ ኃይት ሀውስ መመለስ በፈጠረው ስጋት ምክንያት የኢራን ሪያል ከዶላር አንጻር ያለው ዋጋ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሮይተርስ የምንዛሬ ተመንን የሚከታተለውን ቦንባስት ዶት.ኮም ጠቅሶ እንደዘገበው አንድ ዶላር በ820, 500 እየተመነዘረ ሲሆን ባለፈው አርብ እለት ከነበረው 808,500 ሪያል ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አሳይቷል።