የእስራአል መከላከያ ሚኒስትር ለሀማስ መሪ ሀኒየህ ግድያ ለመጀመሪያ በይፋ ኃላፊነት ወሰዱ
ሀኒየህ ባለፈው ሐምሌ ወር ሀማስ እና የኢራን ባለስልጣናት እስራኤልን ተጠያቂ ባደረጉበት ግድያ ቴህራን ውስጥ ተገድሏል
የሀኒየህ ግድያ በቴህራን እና በቀንደኛ ጠላቷ እስራኤል መካከል ያለውን ውጥረት እንዲባባስ አድርጎታል
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ባለፈው ሐምሌ ውስጥ እስራኤል የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህን ኢራን መግደሏን ለመጀመሪያ ጊዜ በትናንትናው እለት አምነዋል።
የሀኒየህ ግድያ እስራኤል በጋዛ እያደረገች ባለው ጦርነት እና በሊባኖስ ግጭት የተናጋውን በቴህራን እና በቀንደኛ ጠላቷ እስራኤል መካከል ያለውን ውጥረት እንዲባባስ አድርጎታል።
"በአሁኑ ወቅት ወደ እስራኤል ሚሳይል ለሚያስወነጭፈው የሀውቲ የሽብር ድርጅት ግልጽ መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ሀማስን አሸንፈናል፣ ሄዝቦላን አሸንፈናል። የኢራን የሚሳይል መከላከያ ስርአት እንዳይሰራ እና የምርት ስርአቷ እንዲጎዳ አድርገናል፤ በሶሪያም የአሳድን አገዛዝ አሸንፈናል። በቀጣናው ባሉ የሰይጣን ስብስቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰናል። የመን ውስጥ ባለው የሀውቲ የሽብር ቡድን ላይም ከፍተኛ ጉዳት እናደርሳለን "ብለዋል ካትዝ።
እስራኤል "ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎቻቸውን ታውድማለች፤ በሀኒየህ፣ በሲንዋር እና በነስረላህ ላይ በቴህራን፣ ጋዛ እና ሌባኖስ እንደፈጸመችው ሁሉ የመሪዎቻቸውን አንገት ትቆርጣለች" ሲሉካትዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ለማሰብ በተዘጋጅ ስነስርአት ላይ ተናግረዋል።
በኢራን የሚደገፉት የየመን ታጣቃዎች የእስራኤልን የባህር እንቅስቃሴ ለመገደብ በሚል በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከአንድ አመት በላይ አስቆጥሯል።
ሀኒየህ ባለፈው ሐምሌ ወር ሀማስ እና የኢራን ባለስልጣናት እስራኤልን ተጠያቂ ባደረጉበት ግድያ ቴህራን ውስጥ ተገድሏል።
ዋና መቀመጫውን ኳታር ያደረገው ሀኒየህ በተለይ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በተደረጉ አለምአቀፍ የድርድር መድረኮች የሀማስ ፊት ሆኖ አገልግሏል።
ከወራት በኋላ ሀኒየህን በመተካት የሀማስ መሪ የሆነው እና ለአስርት አመታት ባስቆጠረው የእስራኤል- ፍልስጤም ግጭት ውስጥ አዲስ ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆነውን በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል የተባለው ያህያ ሲንዋርን ጋዛ ውስጥ ተገድሏል።
ኢራን የሀኒየህን ግድያ ለመበቀል በበርካታ ባለስቲክ ሚሳይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ፈጽማለች።
እስራኤል ኢራን ለፈጸመችባት ጥቃት በኢራን በወታደራዊ መሰረት ልማት ላይ ጥቃት አድርሳለች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም የሚል ማስጠንቀቂያ ማሰማታቸው ይታወሳል።