ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ተጨማሪ ወታደሮችን እና ድሮኖችን ለማቅረብ እየተዘጋጀች ነው ተባለ
ፕዮንግያንግ ከሞስኮ ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ግንኙነት እየጠነከረ መምጣት የአሜሪካ አጋር ለሆነችው ሴኡል ከባድ ስጋት ሆኗል

ሴኡል፣ ዋሽንግተን እና ኪቭ 12ሺ ገደማ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል
ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ውጊያ እያካሄደች ላለችው ሩሲያ ተጨማሪ ወታደሮች እና ድሮኖች ልትልክ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ማግኘቱን የደቡብ ኮሪያ ጦር በዛሬው እለት አስታውቋል።
ጦር እንደገለጸው ሰሜን ኮሪያ 240 ኤምኤም የተባለ በአንድ ጊዜ በርካታ ሮኬቶችን ማስወንጨፊያዎችን፣ ራሱ መተኮስ የሚችል 170 ኤምኤም የጦር መሳሪዎችን መስጠቷን እና ወደ ሩሲያ የሚላኩ ራሳቸው የሚያጠፉ ወይም 'ሱሳይድ ድሮኞች' ለማምረት ስትዘጋጅ ታይታለች።
"ሱሳይድ ድሮኖችን ማምረት መሪው ኪም ትኩረት ካደረጉባቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው" ያለው ጦሩ ሰሜን ኮሪያ ድሮኖቹን ለሩሲያ የመስጠት ሀሳብ እንዳላት ገልጿል።
እንዲህ አይነት ድሮኖች በዩክሬኑ ጦርነት በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን ኪም አለምአቀፋዊ ፉክክሩ መጠንከሩን በመጥቀስ የአየር ጦር መሳሪያዎች በብዛት እንዲመረቱ ማዘዛቸው ተዘግቧል።
ሴኡል፣ ዋሽንግተን እና ኪቭ 12ሺ ገደማ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የደቡብ ኮሪያ ጦር በኩርስክ ግዛት በተደረገው ውጊያ ቢያንስ 1100 የሚሆኑት ተገድለዋል አለያም ቆስለዋል ብሏል።
ፕዮንግያንግ ከሞስኮ ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ግንኙነት እየጠነከረ መምጣት የአሜሪካ አጋር ለሆነችው ሴኡል ከባድ ስጋት ሆኗል።
ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ቆሻሻ የያዘ ፊኛ በመላክ ጨምሮ የተለያዩ ትንኮሳዎችን በመፈጸም ክስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ፒዮንግያንግ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኘውን የየብስ መንገድ በመቁረጥ እና ምሽግ በማድረግ በሁለት የኮሪያ ባህረ ሰላጤ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ቀጣይነት አሳይታለች።
ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን ከመፈጸማቸው በፊት በአመቱ መጨረሻ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል እንደምታስወነጭፍ እና ጎንለጎን ቆሻሻያ የያዙ ፊኛዎች ወደ ደቡብ ልትልክ ትላለች ተብሏል።