
ሚኒስቴሩ በዚህ ሪፖርቱ የተገደሉትን ሰዎች ንጹሃን እና የታጠቁ ብሎ ባይለይም፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸዉን ከዚህ በፊት ገልጿል
በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 45 ሺ ደርሷል።
እስራኤል በፍልስጤሟ ጋዛ በሚንቀሳቀሰው የሀማስ ታጣቂ ላይ በከፈተችው መጠነሰፊ ዘመቻ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ 45 ሺ ማለፉን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት አስታውቋል።
ከተገደሉት በተጨማሪ 107 ሺ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሳባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ በዚህ ሪፖርቱ የተገደሉትን ሰዎች ንጹሃን እና የታጠቁ ብሎ ባይለይም፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸዉን ከዚህ በፊት ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው እለታዊ መረጃው ባለፈው ቀን 52 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
የሲቪል መከላከያ እና የሆስፒታል ባለስልጣናት እስራኤል በትናንትናው እለት ከባድ የአየር ጥቃት ከተፈጸመባቸው ውስጥ በሰሜን ጋዛ የምትገኘው የጋዛ ከተማ፣ በደቡብ የምትገኘው ካን ዮኒስ ከተማ እንዲሁም በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው ኑሴራት የስደተኞች ካምፕ ይገኙበታል።
እስራኤል የሀማስ ታጣቂዎችን ንጹሃን በሚኖሩበት ቀጣና በመንቀሳቀስ ስትከስ፣ ሀማስ እና የመብት ተሟጋቾች ደግሞ የእስራኤል ጦር ንጹሃንን ለመጠበቅ የሚፈለገውን ያህል አልሰራም ሲሉ ወቀሳ ያቀርባሉ።
ጦርነቱ የተጀመረው ሀማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ የእስራኤልን ደቡባዊ ድንበር ጥሶ በመግባት 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 250 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
አሁን በሀማስ እጅ 100 የሚሆኑ ታጋቾች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1/3 የሚሆኑት ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።
ሀማስ በተመድ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ በሽብርተኝነት ተፈርጇል።
አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር በእስራኤል እና ሀማስ መካካል ያለው ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም እንዲያመራ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት አልተሳካም።