የአሳድ ውድቀት የአሜሪካ እና እስራኤል እቅድ ውጤት ነው - አያቶላ አሊ ሃሚኒ
የሶሪያው መሪ ውድቀት የቴሄራንን የመካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ ሊጎዳው እንደሚችል እየተነገረ ነው
የኢራን ጠቅላይ መሪ የአሳድ አስተዳደር ላይ ሲደረግ የነበረው ውግያ ከአሜሪካ የማዘዣ ክፍል በቀጥታ ትዕዛዝ ሲተላለፍበት ነበር ብለዋል
የሶሪያው መሪ በሽር አላሳድ ውድቀት የእስራኤል እና አሜሪካ እቅድ ውጤት ነው ሲሉ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ሃሚኒ ተናገሩ፡፡
መሪው ከሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ በቀጠናው የምትገኝ በስም ያልጠቀሷት ሀገር ውድቀቱን ለማፋጠን ተባብራለች በማለት ወቅሰዋል፡፡
ሮይተርስ ጠቅላይ መሪው የቀጠናው አንድ ሀገር በሚል በስም ያልጠቀሷት ሀገር ቱርክ መሆኗን በመግለጽ አንካራ የበሽር አላሳድን አስተዳደር በመቃወም ሲዋጉ የነበሩ ታጣቂዎችን ስትደግፍ እንደነበር አመላክቷል፡፡
የአሳድ መንግስት ውድቀት ኢራን የአሜሪካ እና እስራኤልን ተጽዕኖ ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት አጋሮቿን በማመናመን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባት ተገምቷል፡፡
የኢራን መንግስት ሚዲያ እንደዘገበው ሃሚኒ "በሶሪያ የተከሰተው ነገር በሙሉ በዋናነት በአሜሪካ እና እስራኤል ማዘዣ ክፍል ውስጥ በቀጥታ ትዕዛዝ ይተላለፍበት ነበር ለዚህም ማስረጃ አለን፤ በዚህ ሂደትም የሶሪያ ጎረቤት ሀገርም ተሳትፏል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰሜናዊ የሶሪያን ግዛቶች ተቆጣጥራ የምትገኘው የኔቶ አባል ሀገር ቱርክ ከ2011 ወዲህ በአካባቢው የሚገኙ የዋይፒጂ የኩርድ ታጣቂዎች ላይ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ዘመቻዎችን አከናውናለች፡፡
በተጻራሪው ኢራን የአሳድ መንግስትን በስልጣን መዝለቅ ለማረጋገጥ የአብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ወታደሮችን ከማሰማራት አንስቶ በቢሊየን የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
አሳድ ከወደቀ ከሰዓታት በኋላ ኢራን “ከደማስቆ ጋር ያለው ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት አርቆ አሳቢ እና ጥበብ የተሞላበት አካሄድ ላይ በመመስረት እንደሚቀጥል” ገልጻለች፡፡
በተጨማሪም ሁሉንም የሶሪያን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክል ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲቋቋም ጠይቃለች።
ሃሚኒ በንግግራቸው በኢራን የሚመራው ጥምረት በመላው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ላይ ያለው ጠንካራ ተጽእኖም እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።
“ቴሄራን እና አጋሮቿ በተገፉ ቁጥር ይበረታሉ፤ የሚደርስባቻውንም ጫና እጃቸውን አጣጥፈው አይመለከቱም የተረጋጋ አካባቢያዊ ሰላም ይፈጠር ዘንድ የሚችሉትን በማበርከት ይቀጥላሉ” ሲሉም አብራርተዋል፡፡