ካማላ ሃሪስ ቀላል ተፎካካሪ እንዳልሆኑ ባሳዩበት የአሜሪካ ምርጫ ክርክር ማን አሸነፈ?
የፖለቲካ ተንታኞች ዴሞክራቶች በመጀመርያው ዙር ክርክር የጣሉትን ነጥብ በዚህኛው አስመልሰዋል እያሉ ይገኛሉ
የ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች በትላንትናው ምሽት የምርጫ ክርክር አድርገዋል
ለ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ በትላንትናው እለት ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል፡፡
አሁናዊውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እራሳቸውን ከእጩነት እንዲያገሉ ካስገደደው የመጀመርያው ዙር ክርክር በኋላ ሁለቱ እጩዎች ትላንት ምሽት የነበራቸው ቆይታ ውጥረት የተሞላበት እና ከመጀመርያው በተሻለ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለ90 ደቂቃ በቆየው ክርክር በኢኮኖሚ ፣ በህገወጥ ስደተኞች ጉዳይ ፣ በውርጃ ፣ በዩክሬን እና በጋዛ ጦርነት፣ በአጠቃላይ ስትራቴጂ እና ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት አድርገው እጩዎቹ ተከራክረዋል፡፡
ትራምፕ ከባይደን ጋር ካደረጉት ክርክር በብዙ ነጥቦች የተለየ ነበር በተባለው ክርክር ካማላ ሃሪስ የዶናልድ ትራምፕን ትኩረት የሚበታትኑ ግላዊ አጀንዳዎችን አንስተው ወርፈዋቸዋል፡፡
የካፒቶል ሂል አመጽ ፣ ትራምፕ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የሚገኙባቸው ክሶች እንዲሁም በጥቁር አሜሪካውያን እና በነጮች መካከል ክፍፍልን ለመፈጠር ይሻሉ የሚሉ ጉዳዮች ሃሪስ ትራምፕን ለማጥቃት ከመዘዟቸው አጀንዳዎች መካከል ናቸው፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው የጆባይደን እና የካማላ ሃሪስ አስተዳደር አሜሪካ አሁን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ችግር ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳነት የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን የወጣጣበት መንገድ ፣ የዋጋ ንረት እና በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለው ህገወጥ ስደተኛ በባይደን አስተዳደር ጊዜ ወደ አሜሪካ መግባቱን አንስተው አስተዳደሩ ተጨማሪ ጊዜ ሊያገኝ እንደማይገባው ተናግረዋል፡፡
ባይደን አሜሪካን በበቂ ሁኔታ ማስተዳደር አለመቻላቸው ጠላቶቻችን እንዲሳለቁብን አድርጓል ያሉት ትራምፕ በጋዛ እና በዩክሬን የምንመለከተው ጦርነትም የአለም መሪ የሆነችው አሜሪካ በነጩ ቤተ መንግስት ብቃት ያለው መሪ ስሌላት የተከሰተ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በምሽቱ ክርክር አነስተኛ ንግዶችን እንደሚደግፉ ፣ የታክስ ቅናሽ እንደሚያደርጉ ፣የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ እንደሚሰሩ እና ጠንካራ አሜሪካን እንደሚገነቡ ሲናገሩ የተደመጡት ካማላ ሃሪስ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ አስከፊው ፕሬዝዳንት ናቸው ሲሉ ወርፈዋቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ በትራምፕ አስተዳደር ወቅት አብረዋቸው የሰሩ የቀድሞ ባለስልጣናት ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡
ቢቢሲ የምሽቱን የምርጫ ክርክር ማን አሸነፈ በሚል በሰራው ዘገባ ስለ አሸናፊው ለመናገር አሁን ጊዜው ባይሆንም ምክትል ፕሬዝዳንቷ ብልጫ ወሰዷል ማለት ይችላል ብሏል፡፡
ካማላ ሃሪስ ትራምፕ ነጥብ የጣሉባቸውን ወጥመዶች ኮርኳሪ ሀሳቦችን በማንሳት ምላሻ እንዲያጥራቸው አድርገዋል ያለው ዘገባው፤ ዴሞክራቶች በጆ ባይደን ጥለውት የነበረውን ነጥብ በዚህኛው ክርክር ማስመለስ የቻሉ ይመስላል ሲል አስነብቧል፡፡