የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን በመላው ሊባኖስ በሚገኙ ፔጀርስ በተባሉ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎች ላይ ለደረሰው ፍንዳታ ቀንደኛ ጠላቱን እስራኤልን ከሷል
የተገደሉት የሄዝቦላ እና የሀማስ መሪዎች እነማን ናቸው?
በኢራን የሚደገፈው የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን በትናንትናው እለት በመላው ሊባኖስ በሚገኙ ፔጀርስ በተባሉ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎች ላይ ለደረሰው ፍንዳታ ቀንደኛ ጠላቱን እስራኤልን ከሷል።
ይህ ጥቃት የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ እስራኤል ጠላት በምትላቸው ላይ ከፈጸመቻቸው ተከታታይ የግድያ ሙከራዎች ቀጥሎ የተከሰተ ውስብሰብ ዘመቻ ነው ተብሏል።
እስራኤል ተጠያቂ የተደረገችበት የሄዝቦላ እና የሀማስ መሪዎችን እንዲሁም የጦር አዛዦችን ኢላማ ያደረጉት ጥቃቶች የሚከተሉት ናቸው።
ሄዝቦላ
-ፉአድ ሽኩር
እስራኤል ባለፈው ሀምሌ ወር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ደቡባዊ ጫፍ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ፉአድ ሹክር የተባለ የሄዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥን ገድላለች። እስራኤል ሹክር የሄዝቦላ ዋና መሪ የሆነው ሰኢድ ሀሰን ነስረላህ ቀኝ እጅ ነበር ብላለች።
ሄዝቦላ በኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ከአራት አስርት አመታት በፊት ከተቋቋመ ወዲህ ሹክር ከሚታወቁት የሄዝቦላ ወታደራዊ መሪዎች ውስጥ አንዱ ነው።
አሜሪካ በ1983 በቤሩት በሚገኘው የባህር ኃይሏ ካምፕ ላይ በደረሰው እና 241 የአሜሪካ ወታደሮችን በቀጠፈው ፍንዳታ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል በሚል በ2015 በሹክር ላይ ማዕቀብ ጥላበታለች።
ሞሀመዶ ናስ
ሞሀመድ ናስር እስራኤል ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በወሰደችው የአየር ጥቃት ነው የተገደለው። ከደቡብ ምዕራብ ሊባኖስ ወደ እስራኤል የሚተኩሰውን ቡድን ይመራ ነበር ያለችው እስራኤል ለግድያ ኃላፊነት ወስዳለች።
ሮይተርስ ከፍተኛ የሊባኖስ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ናሰር የሄዘቦላን የግንባር ዘመቻዎችን የማስተባበር ኃላፊነት ነበረው።
ታሌብ አብደላህ
ከፍተኛ የፊልድ አዛዥ የሆነው አብደላህ እስራኤል ባለፈው ሰኔ ወር በደቡብ ሊባኖስ በሚገኝ የማዘዥ እና የቁጥጥር ማዕከል ላይ አደርስኩት ባለችው ጥቃት ተገድሏል። ለግድያው እስራኤል ኃላፊነት ወስዳለች።
እንደዘገባው ከሆነ ከናሰር ጋር ተመሳሳይ ማዕረግ ያለው እና የሄዝቦላ የማዕከላዊ ግዛት አዛዥ ነበር።
ግድያው በድኑ በእስራኤል ላይ የሮኬት ናዳ እንዲያስወነጭፍ አነሳስቶት ነበር።
ሀማስ
መሀመድ ዴይፍ
የእስራኤል ጦር የስላላ መረጃን መሰረት በማድረግ ተዋጊ ጀቶች ሐምሌ ወር በጋዛ ውስጥ ካን ዮኒስ አካባቢ ባደረሱት ጥቃት ዴይፍ ተገድሏል።
ዴይፍ ሰባት የግድያ ሙከራዎችን ማምለጥ ችሎ ነበር። ዴይፍ ሀማስ ጥቅምት ወር ድንበር ጥሶ የከፈተውን ጥቃት ካቀነባበሩት ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
እስማኤል ሀኒየህ
የሀማስ የፖለቲካ መሪ የነበረው እስማኤል ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መገደሉን ሀማስ አስታውቋል። ሀኒየህ የተገደለው ባረፈበት የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ላይ በተተኮሰ ሚሳይል ነው። እስራኤል ለግድያው ኃላፊነት አልወሰደችም።
ሳሌህ አል አሮውሪ
እስራኤል ባለፈው ጥር በደቡብ ቤሩት ዳርቻ ደሂየህ ባደረሰችው የድሮውን ጥቃት የሀማስ ምክትል መሪ የሆነው ሳሌህ አል አሮውሪን ገድላለች። አውሮሪ የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድም መስራች ነበር።