ኢራን ሀኒየህ የተገደሉት ካረፈበት ክፍል ውጭ በተተኮሰ የአጭር ርቀት ሮኬት መሆኑን አስታወቀች
የሀማስ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ሀኒየህ የተገደሉት በአዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያኒ በዓለ ሲመት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ነው
ሀኒየህ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ዋና መቀመጫ በሚገኝባት ኳታር በትናንትናው እለት ስርአተ ቁብሩ ተፈጽሟል
ኢራን ሀኒየህ የተገደሉት ካረፈበት ክፍል ውጭ በተተኮሰ የአጭር ርቀት ሮኬት መሆኑን አስታወቀች።
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል(አይአርጂሲ) ወይም የኢራን ጦር የሀማስ ፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ የተገደለው ከነበረበት የእንግዳ ማረፊያ ህንጻ በቅርብ ርቀት በተተኮሰ የአጭር ርቀት ሮኬት መሆኑን አስታውቋል።ጦሩ ለግድያው ከባድ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ በድጋሚ ዝቷል።
የሀማስ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ሀኒየህ የተገደሉት በአዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያኒ በዓለ ሲመት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ነው።
ሀኒየህ ባረፉበት የመንግስት የእንግዳ ማረፊያ ላይ በተቃጣባቸው ጥቃት ሊገደሉ ችለዋል።
ኢራን እና ሀማስ ግድያውን ያደረሰችው እስራኤል መሆኗን ቢገልጹም እስራኤል ግን በጉዳዩ ዙሪያ ያለችው ነገር የለም።
ሀኒየህ፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በሀማስ መሪዎች ላይ ከተፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች ውስጥ በአንዱ ሰለባ ሆኗል።
ይህ ጥቃት በጋዛ በሀማስ እና እስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከቀይ ባህር እስከ ሊባኖስ-እስራኤል ድንበር እና ባሻገር በመለጠጥ ቀጣናዊ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሀኒየህ ግድያ 10 ወራት ያስቆጠሰውን ጦርነት በተኩስ አቁም ለመቋጨት የሚደረገውን አለምአቀፍ ጥረት ይጎዳል ብለዋል።
ግድያው ወደ ተኩስ አቁም የመድረስ እድልን ይጎዳ እንደሆነ የተጠየቁት ባይደን "አይጠቅምም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሀኒየህ የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተካሄዱ ቀጥተኛ ያልሆኑ የተኩስ አቁም ንግግሮች የሀማስ የአለምአቀፍ ዲፕሎማሲ ፊት ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወሳል።
ሀኒየህ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ዋና መቀመጫ በሚገኝባት ኳታር በትናንትናው እለት ስርአተ ቁብሩ ተፈጽሟል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ በእስራኤል ላይ ከባድ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት 40ሺ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል።