የእስራኤል ኢምባሲዎች ከጥቃት እንደማይድኑ የኢራኑ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ
የሁለት የኢራን ጀነራሎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት በተመለከተ እስራኤል አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች
እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው ጥቃት በደማስቆ የሚገኘው የኢራን ቆንስላ ከቀናት በፊት ተመትቷል
የእስራኤል ኢምባሲዎች ከጥቃት እንደማይድኑ የኢራኑ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ።
የእስራኤል ኢምባሲዎች ከጥቃት አይድኑም ሲሉ አንድ ከፍተኛ የኢራን መንግስት ባለስልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራኑ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ አማካሪ የሆኑት ያህያ ራሂም ሳፋቭ ይህን የተናገሩት እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው ጥቃት በደማስቆ የሚገኘው የኢራን ቆንስላ መመታቱን ተከትሎ ነው።
- እስራኤል ሶሪያ ውስጥ በኢራን ቆንስላ ጽ/ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት 2 ጀነራሎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች
- ኢራን በቆንስላዋ ላይ ጥቃት ያደረሰችውን እስራኤልን እበቀላለሁ ስትል ዛተች
ጥቃቱን ተከትሎ ኢራን ጥቃቱን አድርሳለች በተባለችው እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ ስትል ዝታ ነበር።
እስራኤል በበኩሏ ከኢራን ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ መሆኗን እየገለጸች ትገኛለች።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው እለት እንደተናገሩት በሚያዝያ አንዱ ጥቃት ሁለት ጀነራሎቿ የተገደሉባት ጠላቷ ኢራን ልትሰነዝረው የምትችለውን የበቀል እርምጃ ለመመከት በተጠንቀቅ ቆማለች።
የመከለከያ ሚኒስትሩ ዩአብ ጋላንት ጽ/ቤት ይህን መግለጫ ያወጣው ሚኒስትሩ የወታራዊ ዘመቻ ሁኔታን ከከፍተኛ ወታራዊ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ከገመገሙ በኋላ ነው።
"ግምገማው ከተጠናቀቀ በኋላ ሚኒስትር ጋላንት ኢራን ልትሰነዝራቸው ለምትችላቸው ማንኛውም አይነት ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል"ብሏል ጽ/ቤት።
የሁለት የኢራን ጀነራሎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት በተመለከተ እስራኤል አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።
ይሁን እንጅ ሀማስን እና ሄዝቦላን በመርዳት ኢራንን የሚከሱት የእስራኤል መሪዎች ሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን ወታደራዊ ተቋማትን ኢላማ እንደሚታደርጉ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
አሜሪካም ኢራን በቀጣናው ባሉ የእስራኤል ወይም የአሜሪካ ተቋማት ላይ ልታደርስ የምትችለውን ጥቃት ለማክሸፍ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።