እስራኤል የቱርክን አምባሳደር ጠራች
ሀኒየህ፣ የአዲሱን የኢራን መሪ መሱድ ፔዝሽኪያኒን በዓለ ሲመት ለመታደም በሄደበት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ተገድሏል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ባወጡት መግለጫ "የእስራኤል መንግስት እንደ እስማኤል ሀኒየህ ላሉ ገዳዮች ሀዘን መግለጽን አይታገስም" ብለዋል
እስራኤል የቱርክን አምባሳደር ጠራች።
በእስራኤል የሚገኘው የቱርክ ኢምባሲ፣ የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ግድያን ለማሰብ ሰንደቅአላማውን ዝቅ አድርጎ ማውለብለቡን ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የቱርክን ምክትል አምባሳደር ጠርቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ባወጡት መግለጫ "የእስራኤል መንግስት እንደ እስማኤል ሀኒየህ ላሉ ገዳዮች ሀዘን መግለጽን አይታገስም" ብለዋል።
ሀኒየህ፣ የአዲሱን የኢራን መሪ መሱድ ፔዝሽኪያኒን በዓለ ሲመት ለመታደም በሄደበት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ባረበፈት የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ላይ በተቃጣ ጥቃት ተገድሏል።
እስራኤል ለግድያው በይፋ ኃላፊነት ባትወስድም፣ ኢራን እና አጋሮቿ ሀማስ እና ሄዝቦላን ጨምሮ እስራኤልን ግድያውን በመፈጸም ከሰዋል፤ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱም ዝተዋል።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን ባለፈው አርብ ለሀኒየህ የሀዘን ቀን ሆኖ እንዲውል አውጀዋል።
የካቲዝ መግለጫ እንዳስታወቀው ሀኒየህ ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ በ50 አመታት ውስጥ ከባድ የተባለውን ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን በገደለበት እና 250 ሰዎችን አግቶ በወሰደበት ወቅት መሪ ነበር።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦንሱ ከሰሊ ለካትዝ መግለጫ "ተደራዳሪዎችን በመግደል እና ዲፕሎማቶችን በማስፈራራት ሰላም አታመጣም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከ39ሺ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበት የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል እና በቱርክ መካከል ያለው ውጥረት አይሏል። እስራኤል በጋዛ ግፍ እየተፈጸመች ነው የምትለው ቱርክ፣ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል።