አረብ ኤምሬትስ 80 ቶን የሰብአዊ እርዳታ ለሊባኖስ ሰጠች
በሊባኖስ በእስራኤል -ሄዝቦላ ግጭት ምክንያት ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል
የሰብአዊ እርዳታ የያዙ ሁለት የአረብ ኢምሬትስ አውሮፕላኖች ቤይሩት ኤየርፖርት አርፈዋል
አረብ ኢምሬትስ 80 ቶን የሚሆን የሰብአዊ እርዳታ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው ለሊባኖስ ሰጠች።
"አረብ ኢምሬትስ ከሊባኖስ ጋር ነች" በሚለው ዘመቻ በሁለት አውሮፕላኖች የተጫነ የሰብአዊ እርዳታ ቤይሩት ኤርፖርት ደርሷል።
ይህ እርዳታ የተበረከተው "የኢምሬቶች እናት" ተብለው ከሚጠሩት እና የሴቶች ህብረት ሊቀመንበር፣ የሴቶችና ህጻናት ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ከሆኑት ሸኪና ፋጢማ ነው።
80 ቶን የእርዳታ ቁሳቁሶች የያዙ ሁለት አውሮፕላኖች በችግር ውስጥ ለሚገኙት የሊባኖስ እናቶች ደርሰዋል።
የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝደንት ሸክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ አረብ ኢምሬትስ "ኢምሬትስ ከሊባኖስ ጋር ነች" በሚለው ዘመቻ እርዳታ ማቅረቧን ትቀጥላለች ብለዋል።
እስራኤል እና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላ ጋር ወደ ቀጥተኛ ግጭት ገብታለች።
ለአንድ አመት ያህል ከፍልስጤሙ ታጣቂ ጋር በጋዛ ጦርነት ስታደርግ የነበረችው እስራኤል አሁን ትኩረቷን ወደ ሄዝቦላ አዙራ በእግረኛ ጦር እና በአየር ኃይል ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመች ነው።
እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህ እና እሱን ይተካዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሀሽም ሰይፈዲን ተገድለዋል።
እስራኤል ጥቃቷ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ብትገልጽም፣ ሄዝቦላ ግን ንጹሃን ሰለባ ሆነዋል ሲል ይከሳል።
በጦርነቱ ምክንያት በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ተሰደው ሰብአዊ እርዳታ ለመጠበቅ ተገደዋል ተብሏል።