ትራምፕ ለኢራኑ ሃሚኒ የኒዩክሌር ድርድር ለመጀመር ደብዳቤ ላኩ
"የኢራን ጉዳይ በወታደራዊ አልያም በስምምነት ሊፈታ ይችላል፤ እኔ ግን ኢራናውያንን ላለመጉዳት ስምምነት ላይ መድረስን እመርጣለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ

ሩሲያ ከ2018 ወዲህ ዳግም ግንኙነታቸው የሻከረውን ዋሽንግተን እና ቴህራን ለማሸማገል ጥሪ ማቅረቧ ተገልጿል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የኒዩክሌር ድርድር ለመጀመር ለኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በይፋ ደብዳቤ መላካቸውን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቴህራን ዳግም ወደ ንግግር ትመለሳለች ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
"የኢራን ጉዳይ በሁለት መንገዶች ሊፈታ ይችላል፤ በወታደራዊ አልያም ስምምነት ላይ በመድረስ፤ እኔ የኢራን መልካም ህዝብ እንዳይጎዳ ስምምነቱን እመርጣለሁ" ሲሉም ነው ያብራሩት።
የኢራን ባላንጣ የሆነችው እስራኤል ስትራቴጂካዊ አጋር አሜሪካ ቴህራን ወደ ድርድር ተመልሳ ስምምነት ካልፈረመች ምን ሊፈጠር እንደሚችል በዝርዝር ባይጠቅሱም "ሌላ ኒዩክሌር የታጠቀ ሀገር እንዲኖር አንፈቅድም" ብለዋል።
ኢራን በትራምፕ ተልኳል ስለተባለው የድርድር እንጀምር ደብዳቤ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው (2018) ኢራን ከአምስቱ የጸጥታው ምክርቤት ቋሚ አባላት እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በፈረንጆቹ 2015 ከተፈራረመችው የኒዩክሌር ስምምነት ሀገራቸውን አስወጥተው በቴህራን ላይ ዳግም ማዕቀቦች እንዲጣሉ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በመላው አለም የተጀመሩ ግጭቶችና ጦርነቶችን በማስቆም "ሰላም ሰሪ መሪ" በመባል በታሪክ መወሳት እፈልጋለሁ የሚሉት ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት እንደገቡ ከቴህራን ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።
"ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆን የለባትም" ሲሉም በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ቴህራን በበኩሏ ለትራምፕ ሁለት አይነት መልሶችን ስትሰጥ ቆይታለች። የሀገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ "ትራምፕ ስምምነቱን (የ2015ቱን የኒዩክሌር ስምምነት) ቀዶ ጥሎታል፤ ከአሜሪካ ጋር መደራደር እንደማያዋጣ በልምድ አረጋግጠናል" ባይ ናቸው።
ለዘብተኛው ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ዋሽንግተን የሁለቱንም ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት የምታቀርብ ከሆነ ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በቻይና አደራዳሪነት ከቴህራን ጋር ግንኙነቷን ለማደስ የተስማማችው ሳኡዲ አረቢያ በቅርቡ አሜሪካ እና ኢራንን ለማቀራረብ ፍላጎት እንዳላት ማስታወቋ ይታወሳል።
የቴህራን አጋር ሩሲያም ዋሽንግተን እና ቴህራንን ለማሸማገል ጥሪ ማቅረቧ ተዘግቧል።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርኬ ራያብኮቭ ከኢራን አምባሳደር ካዘም ጃላኒ ጋር ሲመክሩ ክሬምሊን ኒዩክሌር የሚያነታርካቸውን ሀገራት ለማስማማት ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።