ኢራን ለሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መላኳ ተሰማ
ኢላማቸውን አይስቱም የተባሉት የቴህራን ሚሳኤሎች ሩሲያ በዩክሬን በምታካሂደው ጦርነት ድል እንድትቀዳጅ በእጅጉ ያግዟታል ተብሏል
ኢራን ድሮኖች እና ሚሳኤሎችን እንዳትሸጥ በጸጥታው ምክርቤት የተጣለባት ክልከላ በጥቅምት ወር 2023 ማብቃቱ ይታወሳል
ኢራን ለሩሲያ 400 የሚጠጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ለማቅረብ ተስማምታ ወደ ሞስኮ መላክ መጀመሯ ተነገረ።
ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ የኢራን ምንጮቼ አረጋገጥኩ ብሎ እንደዘገበው፥ ቴህራን ባለፉት ሳምንታት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ሞስኮ እየላከች ነው።
“ፋቴህ 110” በሚሰኘው የአጭር ርቀር ባለስቲክ ሚሳኤል የሚመደቡ እንደ “ዞልፋጋር” አይነት ሚሳኤሎች ናቸው ለሩሲያ በካስፒያን ባህር እና በአውሮፕላን እየቀረቡ የሚገኙት።
ከ300 እስከ 700 ኪሎሜትሮች የሚምዘገዘጉት ባለስቲክ ሚሳኤሎች ኢላማቸውን በተሳካ ሁኔታ በመምታት የተመሰከረላቸው ናቸው ተብሏል።
የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ባለፈው አመት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያወሳው ሬውተርስ የሚሳኤሎቹ ጭነት በጥር ወር መጀመሪያ መጀመሩን ምንጮቹ እንደነገሩት ገልጿል።
ኢራንም ሆነች ሩሲያ ግን ስለባለስቲክ ሚሳኤሎቹ ሽያጭ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ኢራን ድሮን እና ሚሳኤል ለሌሎች ሀገራት እንዳትሸጥ ያስቀመጠው ክልከላ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ማብቃቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም ላይ የጣሉት ማዕቀብ እስካሁን አልተነሳም። ቴህራን መሳሪያዎቿን ወደ ሩሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ አጋሮቿ መላኳ ስጋት ይፈጥርባቸዋል።
ከሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎችን በማግኘት ላይ የምትገኘው ሩሲያ ከኢራን የሚላክላት ባለስቲክ ሚሳኤል በዩክሬኑ ጦርነት በፍጥነት ድል እንድትቀዳጅ ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል።
የአሜሪካው የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢም ሞስኮ ከቴህራን እና ፒዮንግያንግ የሚላኩላት ሚሳኤሎች ዋሽንግተንን ያሳስባል ማለታቸው አይዘነጋም።
ዩክሬንም የኢራን ባላስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ ስለመግባታቸው እስካሁን ማረጋገጥ ባልችልም ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ ነው ብላለች።
ኬቭ “ሻሄድ” የተሰኙ የኢራን ድሮኖች የዩክሬን መሰረተ ልማቶችን በማፈራረስ ቀዳሚ እንደሆኑ ስትገልጽ ቆይታለች።
ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መጀመር በኋላ ይበልጥ ያደገው የኢራንና ሩሲያ ወታደራዊ ትብብር በቅርቡ የሀገራቱ መሪዎች በሚፈራረሙት ሰፊ የትብብር ስምምነት እንደሚጠናከር ይጠበቃል።
ለሞስኮ ድሮኖች እና ባለስቲክ ሚሳኤሎችን የላከችው ቴህራን በምትኩ ኤስዩ -35 ተዋጊ ጄቶች እና ኤምአይ -28 የውጊያ ሄሊኮፕተሮችን እንደምታገኝ ተዘግቧል።