ኢራን በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ባንኮችና የመንግስት ተቋማትን ዘጋች
ቴህራንን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሙቀት ተመዝግቧል
በሙቀቱ ምክንያት ከ200 በላይ ሰዎች ታመው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፥ ለማቀዝቀዣዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታው ጨምሯል ተብሏል
በኢራን ባንኮች፣ የመንግስት ተቋማትና የፋይናንስ ገበያዎች በዛሬው እለት ዝግ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በሀገሪቱ የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከባድ የህብረተሰብ ጤና ችግር እንዳይፈጥርና ሃይል ለመቆጠብ በሚል ነው ሁሉም የመንግስትና የንግድ ተቋማት ዝግ ሆነው እንዲውሉ የተወሰነው።
በመዲናዋ ቴህራን በትናንትናው እለት 42 ዲግሪ ሴልሺየስ የሆነ ሙቀት መመዝገቡን የኢራን ብሄራዊ የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።
የሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ መከላከል ቢሮ በከባድ ሙቀቱ ምክንያት 225 ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውና አፋጣኝ ህክምና እንደሚሹ ነው ያስታወቀው።
በኢራን 10 ግዛቶች በትናንትናው እለት 45 ዲግሪ ሴልሺየስ የደረሰ ሙቀት ተመዝግቧል።
ከፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ጋር በምትዋሰነው ደልጋን 49 ነጥብ 7 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኖ የተመዘገበው ሙቀትም ከፍተኛው መሆኑን የሀገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ገልጿል።
የሙቀት መጠኑ ከነገ ጀምሮ እየቀነሰ እንደሚሄድ ቢጠበቅም ኢራናውያን በቤት ውስጥ የአየር ማቀዝቀዣዎችን በመጠቀም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ነው ያሳሰበው።
በከባዱ ሙቀት ምክንያት ለማቀዝቀዣዎች የሚውል የኤሌክትሪክ ፍጆታ ጨምሯል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተመዘገበው 78 ሺህ 106 ሜጋዋት የሃይል ፍጆታም ከፍተኛው ነው መባሉ ተዘግቧል።
በኢራን ባለፉት 50 አመታት የተመዘገበው ሙቀት በአለማቀፍ ደረጃ ሙቀት ከሚጨምርበት በእጥፍ እንደሚልቅ የሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ይፋ ማድረጉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ቴህራን ባለፈው አመትም በሙቀት መጨመር ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት የእረፍት ቀናት ማወጇ የሚታወስ ነው።