በፈረንሳይ በባቡር ሀዲዶች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ የኢራን እጅ እንዳለበት እስራኤል ገለጸች
እስራኤል ስለታቀደው ጥቃት ለፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መስርያ ቤት ቀደም ብሎ ጥቆማ መስጠቷን አስታውቃለች
ቴልአቪቭ ላቀረበችው ውንጀላ ኢራን እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጠችም
በትናንትናው እለት በመላው ፈረንሳይ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ከሆነው ጥቃት ጀርባ ኢራን እንዳለችበት እስራኤል አስታወቀች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትረ እስራኤል ካትዝ ጥቃቱን በማቀነባበር ኢራን ዋነኛዋ ተዋናይ ናት ብለዋል።
በተጨማሪም ቴሄራን ተጨማሪ የሽብር ጥቃቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ ላይ እንዲፈጸሙ ለሽብርተኛ ቡድኖች ድጋፍ እያደረገች እንደሚገኝ የደህንነት ተቋሞቻችን መረጃ አመላክቷል ነው ያሉት።
አክለውም ጥቃቱ ሊፈጸም እንደሚችል ለፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስቴፋን ሰጆርኔ በመደወል ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ስለማጋራታቸው ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ፈረንሳይ ልትወስድ እንደሚገባም መናገራቸውን አርቲ ዘግቧል።
እስራኤል ላቀረበችው ውንጀላ ኢራን እስካሁን ይፋዊ ምልሽ አልሰጠችም ሆኖም የሀገሪቱ ጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለማወቅ ምርመራ ላይ መሆናቸውን ከማሳወቅ ውጪ በይፋ የተጠርጣሪዎችን ማንነት አላሳወቁም።
የሀገሪቱ ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት እንዳስታወቀው ሆን ተብሎ በባቡር ሀዲዶቹ ላይ በተፈጸመ ከባድ ጥቃት ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጧል፡፡
በዚህም ወደ ፈረንሳይ ሶስት ትላልቅ ከተሞች የሚደረጉ ጉዞች ሙሉ ለሙሉ የተቋረጡ ሲሆን እስከሳምንቱ መጨረሻ ድረስ 800 ሺህ የሚጠጉ ተጓዦች በአደጋው ጉዟቸው እንደሚስተጓጎል ተነግሯል፡፡
ቀደም ብለው በወጡ መረጃዎች አይኤስ አይኤስ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ላይ ጥቃት ለመፈጸም በቲክቶክ እና በሌሎች ድረ ገጾች ወጣቶችን እየመለመለ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነትን ተከትሎ በመላው አውሮፓ የሽብር ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ሲነገር በተያዘው አመት የደረሱ እና ለመፈጸም የታሰቡ የሽብር ጥቃቶች በ2022 ከነበረው በአራት እጥፍ መጨመራቸው ተሰምቷል፡፡
በአውሮፓ ባለፉት 9 ወራት ከቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ 58 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከነዚህ መካከል 38ቱ ከ13-19 እድሜ ላይ የሚገኙ ታዳጊ እና ወጣቶች መሆናቸው ነው የተሰማው፡፡
ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአውሮፓ 27 የሽብር ጥቃቶች እና ሽብር ለመፈጸም ሲሸረቡ የነበሩ ሴራዎች እንደነበሩ ተደርሶበታል፡፡