ኢራን ወታደራዊ ሃይሏን ወደ ሊባኖስ እንደማትልክ ገለጸች
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄዝቦላህም ሆነ ሃማስ “የእስራኤልን ወረራ የመመከት አቅም አላቸው፤ የድጋፍ ጥያቄም አልቀረበልንም” ብሏል
ወታደራዊ አመራሮቿ በቤሩት ከናስራላህ ጋር የተገደሉባት ቴህራን በቴል አቪቭ ላይ የምትወስደው የአጻፋ እርምጃ ግን አይቀሬ መሆኑን አስታውቃለች
ኢራን በሊባኖስ እስራኤልን ለመዋጋት ወታደራዊ ሃይሏን እንደማትልክ አስታወቀች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ “የኢራን በጎ ፈቃደኞችን ወደ ሊባኖስም ሆነ ወደ ጋዛ መላክ አይጠበቅብንም” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ሄዝቦላህም ሆነ ሃማስ “የእስራኤልን ወረራ የመመከት ብቃት አላቸው፤ ከቡድኖቹ የቀረበልን የድጋፍ ጥያቄ የለም፤ የኛን ድጋፍ እንደማይሹም አረጋግጠናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ቴህራን በግዛቷ ለተገደሉት የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያ ተጠያቂ ባደረገቻት ቴል አቪቭ ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ስትዝት ቆይታለች።
እስራኤል ባለፈው አርብ በሊባኖስ መዲና ቤሩት የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህን በገደለችበት ጥቃት የኢራን ቁድስ ሃይል ከፍተኛ አዛዥ አባስ ኒልፎሩሻን ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎም የአጻፋ እርምጃ እንወስዳለን ዛቻው ከተለያዩ የቴህራን ባለስልጣናት ሲደመጥ ነበር።
እስራኤል በኢራን ድጋፍ ይደረግላቸዋል በሚባሉ የሊባኖስ፣ የመን እና ሶሪያ ሃይሎች ላይ የምትወስደውን እርምጃ ባጠናከረችበት ወቅት ከወደ ቴህራn ዛሬ የተሰማው ከተለመደው ለዘብ ያለ ነው ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ናስር ካናኒ ግን ቴህራን ወደ ሊባኖስ እና ጋዛ ወታደሮቿን አትልክም መባሉ በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የአጻፋ እርምጃ ሰርዛዋለች ማለት አይደለም ማለታቸውን አል አይን አል አክባሪያ ዘግቧል።
የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጀነራል አብዶልራሂም ሙሳቪም ለናስራላህ ግድያ የሚወሰደው የአጻፋ እርምጃ “በቅርቡ ይፈጸማል” ሲሉ ተናግረዋል።
የጦር አዛዡ በቴህራን በሚገኘው የሄዝቦላህ ቢሮ በመገኘት ሀዘናቸውን ከገለጹ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “የሄዝቦላህ ሰንደቅ አልወረደም፤ በእያንዳንዱ መስዋዕት ደም የቡድኑ ሰንደቅ ከፍ ብሎ ይውለበለባል፤ ነገ ከዛሬ በተሻለ ከፍ ይላል” ብለዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያንም በሄዝቦላህ የቴህራን ቢሮ ተገኝተው ሀዘናቸውን መግለጻቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በኢራን ወሳኝ ጉዳዮች የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉት አያቶላህ አሊ ሃሚኒ፥ በቤሩት የተገደሉት የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀር ከሰሞኑ ደጋግመው ገልጸዋል።
በቴህራን ህይወታቸው ላለፈው ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያ የአጻፋ እርምጃ እወስዳለሁ ካለች ወራት ያስቆጠረችው ቴህራን በእስራኤል ላይ መቼና እንዴት ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል ከመግለጽ ተቆጥባለች።