የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች ወታደራዊ ሚስጥር እየሰረቁ መሆናቸውን አሜሪካ እና አጋሮቿ ገለጹ
የመረጃ ጠላፊዎቹ ሆስፒታሎችን እና የጤና ተቋማትን የኮምፒውተር ስርአት በመስበር ገንዘብ መውሰዳቸው ተገልጿል
በሳይበርሴኩሪቲ ተመራማሪዎች ኤፒቲ45 ተብለው የሚጠሩት መረጃ ጠላፊዎቹ ከሰሜን ኮሪያ የስለላ ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዳለው እንደሚታመን ተገልጿል
የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች ወታደራዊ ሚስጥር እየሰረቁ መሆናቸውን አሜሪካ እና አጋሮቿ ገለጹ።
የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች እግድ ለተጣለበት የፒዮንግያንግ የኑክሌር ፕሮግራም ሊረዳ የሚችል መረጃ ለማግኘት አለምአቀፍ የስለላ ዘመቻ መክፈታቸውን አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ደቡብ ኮሪያ በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።
በሳይበርሴኩሪቲ ተመራማሪዎች ኤፒቲ45 ተብለው የሚጠሩት መረጃ ጠላፊዎቹ በአሜሪካ በፈረንጆቹ 2015 ማዕቀብ ከተጣለበት ሪኮኔሳንስ ጀነራል ቢሮ ከተባለው የሰሜን ኮሪያ የስለላ ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዳለው እንደሚታመን ተገልጿል።
ይህ የሳይበር ቡድን የታንክ ማምረቻዎችን፣ ባህር ሰርጓጇችን፣ የባህር ኃይል መርከቦችን፣ ተዋጊ ጀቶችን፣ ሚሳይሎችን እና የራዳር ስርአቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከያ እና የኢንጂነሪንግ ተቋማትን ኢላማ እያደረገ እና እየበረበረ እንደሚገኙ መግለጫው ጠቅሷል።
በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙት የናሽናል ኢሮኖቲክስ እና ስፔስ አስተዳደር(ናሳ)፣ በቴክሳስ የሚገኘው ራንዶልፍ ኤየር ፎርስ ቤዝ የመረጃ ጠለፋ ሰላባ ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ(ኤፍቢአይ) እና የፍትል ሚኒስትር በትናንትናው እለት አስታውቋል።
በፈረንጆቹ የካቲት 2022፣ ናሳን ኢላማ ያደረጉ የመረጃ ጠላፋዎች ማልዌር በመጠቀም የኮምፒውተር ስርአቱን ለሶስት ወራት ሳይበረብሩ እንዳልቀሩ የአሜሪካ አቃቤ ህግ ጥርጣሪ አለው።
መግለጫው "ቡድኑ እና የሳይበር ቴክኒኮች በመላው አለም በሚገኙ ተቋማት ላይ ስጋት ደቅነዋል" ብሏል።
በአለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መገለል ውስጥ ያለችው እና ቀደም ሲል ዲሞክራቲክ ፒፕልስ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮሪያ (ዲፒአርኬ) የመረጃ ጠላፊዎችን በመጠቀም ጥብቅ ወታደራዊ ሚስጥሮችን የመስረቅ ታሪክ አላት።
የመረጃ ጠላፊዎቹ ይህን ተግበራቸውን የሚረዳ ገንዘብ ለማግኘት የአሜሪካ ሆስፒታሎችን እና የጤና ተቋማትን የኮምፒውተር ስርአት በመስበር ገንዘብ በማጭበርበር መውሰዳቸውን ተገልጿል።
ኤፍቢአይ እና የፍትህ ሚኒስቴር 600 000 ዶላር ቪርቹዋል ገንዘብ ያለውን አካውንት ጨምሮ የተወሰኑ ጠላፋዎችን አካውንት መያዛቸውን እና ለተጠቂዎቹ እንደሚመልሱ ተናግረዋል።