በቤሩት ጥቃት የተገደለው ተፈላጊው የሂዝቦላህ አዛዥ ኢብራሂም አቂል ማን ነው?
አሜሪካ ኢብራሂም አቂል ያለበትን ለጠቆመኝ 7 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ብላ ነበር
ኢምራሂም አቂል በአሜሪካ እና በእስራል ላይ ከተፈጸሙ ትላልቅ ጥቃቶች ጀርባ የነበረ ሰው ነው
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በደቡባዊ ቤሩት በፈጸመው የአየር ጥቃት የሂዝቦላህ ወታደራዊ አዛዥ ኢብራሂም አቂልን መግደሉን አስታውቋል።
የሂዝቦላህ አዛዥ ኢብራሂም አቂልን ኢላማ አድርጎ በተፈጸመ ጥቃት የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 66 ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
ኢብራሂም አቂል ተገደለው ከእስራኤል F-35 ጄት በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች ሲሆን፤ በወቅቱም ኢብራሂም ከሌሎች የሄዝቦላህ አመራሮች ጋር በስብሰባ ላይ ነበር ተብሏል።
የእስራኤል ጦር ቃል ቀባይ በአየር ጥቃቱ የሂዝቦላህ የሬድዋን ሀይል ኮማንደር የሆነው ኢብራሂም አቂል መገደሉን ተናግረዋል።
መጀመሪያ ላይ ወታራዊ መሪው መገደሉን አጣጥሎ የነበረው ሂዝቦላህ፤ በኋላ ላይ የሬድዋን ሀይል ኮማንደር የሆነው ኢብራሂም አቂል በእስራኤል ጥቃት መገደሉን አረጋግጧል።
የእስራኤል ጥቃት ኢላማ የነበረው ኢብራሂም አቂል ማን ነው?
ኢብራሂም አቂል በብዛት ሃጂ ታሰን በሚል ስሙ የሚታወቅ ሲሆን፤ በቤሩት የአሜሪካ ኤምባሲ የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በሊባኖስ የነበሩ የአሜሪካ ባህር ኃይል አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ ይፈለግ ነበር።
ኢብራሂም አቂል በፈረንቹ 1983 በቤሩት የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት እና 63 ሰዎችን በገደለው የሽብር ተግባር ዋና ተጠያቂ መደረጉ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ዓመት በፈረንጆቹ 1983 ጥቅምት ወር ላይ በሊባስ በሚገኙ የአሜሪካ ባር ኃሎች ኢላማ ባደረገ እና 241 የአሜሪካ ወታደሮች በተገደሉበት ጥቃት ላይም እጁ አለበት ተብሏል።
ሂዝቦላህ የአሜሪካ እና የጀርመን ዜጎችን ባገተበት ቅትም ኢብራሂም አቂል የተለያዩ ዘመቻዎችን ሲመራ የነበረ ቁልፍ ሰው ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ኢብራሂም አቂል በእስራኤል በፈረንጆቹ 2019 እና 2023 የተፈጸሙ ጥቃቶችን አስተባብሯል የተባለ ሲሆን፤ ሄዝቦላህ በሰሜን እስራኤል በኩል የሚያደርጋቸውን ውጊያዎች ከሚመሩ ሰዎች መካልም ቀዳሚው እንደነበረ ይገርለታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢብራሂም አቂልን በተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ አካቶ የቆየ ሲሆን፤ ያለበትን ለጠቆመኝ 7 ሚሊየን ዶላር እከፍላልሁ ብሎም ነበር።
እስራኤል የሂዝቦላህ ከፍተኛ አመራር መካከል ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ፉአድ ሽኩርን በደቡባዊ ሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል።