አሜሪካ በኢራን ምክንያት ለቀድሞው ባለስልጣን ደህንነት በየወሩ 2 ሚሊዮን ዶላር እየከፈለች ነው
ኢራን በቀድሞው የዋሽንግተን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ላይ ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል ተሰግቷል
ማይክ ፖምፒዮ እና በቴህራን የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ብሪያን ሁክ የኢራን ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል
አሜሪካ በኢራን ምክንያት ለቀድሞው ባለስልጣን ደህንነት በየወሩ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እየከፈለች ነው።
አሜሪካ እና ኢራን ግንኙነታቸው በየጊዜው ግንኙነታቸው እየተበላሸ የመጣ ቢሆንም በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአስተዳድር ዘመን በኢራን አብዮታዊ ዘብ ጦር መሪ ቃሲም ሱሊማኒ መገደል በኋላ ግን ግንኙነታቸው ተባብሷል።
ኢራን ለዚህ የአሜሪካ ግድያ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደምትወስድ መዛቷን ተከትሎ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፒዮ እና በቴህራን የዋሽንግተን አምባሳደር የነበሩት ብሪያን ሁክ ላይ ኢራን ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ተሰግቷል።
ስጋቱን ተከትሎም ሁለቱ የቀድሜ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች መንግስት ልዩ የደህንነት ጥበቃ እያደረገላቸው እንደሆነ ኤፒ ዘግቧል።
አሜሪካ ለነዚህ ዲፕሎማቶች ደህንነት ጥበቃ በወር ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ላይ ነውም ተብሏል።
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ኢራን ማይፕ ፖምፒዮን እና ብሪያን ሁክን ለመግደል እያሴረች እንደሆነ ገልጿል።
ይሄንን ተከትሎም የፕሬዝዳንድ ባይደን አስተዳድር ለሁለቱ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ፈቅዷል።
አሜሪካ ኢራን ከተቀረው ዓለም እንድትነጠል እና የንግድ ግንኙነቷ እንዲቋረጥ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን መጣሉ ይታወሳል።
ከሰሞኑም የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጦር በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ረቂቅ በማዘጋጀት ላይ መሆኗ ተገልጿል።