ቴህራን በበኩሏ በኢስፋሃን ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ፋብሪካ ላይ ጥቃት ለማድረስ የተላኩ ድሮኖችን መታ መጣሏን ገልጻለች
በኢራን ወታደራዊ ፋብሪካ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የእስራኤል እጅ እንዳለበት የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ኢስፋሃን በተሰኘችው ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን ፋብሪካ በሶስት ድሮኖች ነው ለማጥቃት የተሞከረው። ቴህራን ግን ድሮኖቹን መታ መጣሏን እና የከፋ ጉዳትም እንዳልደረስ ገልጻለች።
ፍንዳታው መጠነኛ ጉዳት አድርሷል ያለው የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር፥ የጉዳቱን መጠን ግን አላብራራም። የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃንም ጥቃቱን ያደረሱ ድሮኖች መመታታቸውን ያሳያል ያሉትን የቪዲዮ ምስል አጋርተዋል።
የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች በፋብሪካው ዙሪያ በብዛት ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውም የደረሰው ጉዳት “መጠነኛ” አለመሆኑን ያመላክታል እየተባለ ነው።
ከዚህ ጥቃት ጀርባም የኢራን የረጅም ጊዜ ባላንጣ እስራኤል እንዳለችበት የአሜሪካ ባለስልጣናት ነገሩኝ ብሎ ሬውተርስ ዘግቧል።
ወልስትሪት ጆርናልም ስማቸውን ካልጠቀሳቸው ምንጮች ቴል አቪቭ ለጥቃቱ ተጠያቂ መሆኗን ማረጋገጡን አስነብቧል።
የዋይትሃውስ ባለስልጣናት ዋሽንግተን ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላት ግን መግለጻቸውን ዘገባው አክሏል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ሬይደር፥ በድሮን ጥቃቱ ዙሪያ አሜሪካ እጇ እንደሌለበት ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ማብራሪያን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናትም ለቀረበው ወቀሳ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ወር ዳግም ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በቴህራን ላይ የድሮን ጥቃት በመፈጸም የተወቀሱት።
ጥቃቱ የተፈጸመባት ኢስፋን ከተማ በርካታ የኢራን የኒዩክሌር ጣቢያዎች የሚገኙባት ናት።
እስራኤል በነዚህ የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያዎች ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጓን ኢራን ትገልጻለች።
ባለፈው አመት ሃምሌ ወር ላይም በኢስፋን የሚገኘውን ግዙፍ ወታደራዊ ፋብሪካ ለማፈራረስ ከቴል አቪቭ ጋር እያሴሩ ነው ያለቻቸውን የኩርድ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ማዋሏን መግለጿ የሚታወስ ነው።