ስምምነቱ የሻከረውን የሀገራቱን ግንኙነት ያለሳልሳል ተብሏል
ዋሽንግተንና ቴህራን ከረጅም ድርድር በኋላ 10 እስረኞችን ተለዋውጠዋል።
ኳታር ባሸማገለችው ድርድር ሁለቱ ሀገራት አምስት፣ አምስት እስረኞችን የተለዋወጡ ሲሆን፤ በአሜሪካ ተይዞ የነበረው ስድስት ቢሊዮን ዶላር የኢራን ገንዘብም በስምምነት ተለቋል።
የኢራን መንግስት ገንዘቡ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከተላከ በኋላ በቴህራን እጅ ሰኞ እንደሚገባ አስታውቋል።
በቴህራን የኒውክሌር መርሀ-ግብርና በሌሎችም ጉዳዮች ውጥረት ውስጥ የገቡት ሀገራቱ፣ ከወራት ድርድር በኋላ ስምም ላይ ደርሰዋል።
ጥምር ዜግነት ያላቸው አምስቱ አሜሪካዊያን እስረኞች ከኢራን ወደ ዶሀ ካቀኑ በኋላ ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ ተብሏል።
በልውውጡ አምስት በአሜሪካ የታሰሩ ኢራናዊያን ይለቀቃሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባዩ ሁለቱ እስረኞች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ፤ ሁለቱ ደግሞ ባቀረቡት ጥያቄ እዛው አሜሪካ ይቆያሉ ብለዋል። አንዱ እስረኛ ወደ ሦስተኛ ሀገር እንደሚጓዙ ገልጸዋል።
ስምምነቱ ዋሽንግተን የሽብር ሀገር ስትል ከበየነቻት ቴህራን ጋር ያላትን ግንኙነት ያለሳልሳል ተብሏል።
ሆኖም በኢራን የኒውክሌር መርሀ-ግብር፣ በቀጣናው ባላት ተጽዕኖና በሌሎችም ጉዳዮች ሀገራቱ ሆድና ጀርባ ናቸው።