ኢራን ከሞስኮው ጥቃት በፊት ለሩሲያ የደህንነት ስጋት መረጃ አጋርታ ነበር ተባለ
በፈረንጆቹ መጋቢት 22 የተቃጣው ይህ ጥቃት በሁለት አስርት አመታት ውስጥ በሩሲያ ምድር የተፈጸመ ከባድ ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል
በሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ላይ ጥቃት ከመድረሱ ቀደም ብላ በሩሲያ ምድር ላይ ትልቆ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ሩሲያን አስጠንቅቃ ነበር ተብሏል
ኢራን ከሞስኮው ጥቃት በፊት ለሩሲያ የደህንነት ስጋት መረጃ አጋርታ ነበር ተባለ።
ኢራን በዚህ አመት መጀመሪያ ከባድ የቦምብ ጥቃት ባደረሱ ሰዎች ላይ ባደረገችው ምርመራ ያገኘችውን መረጃ ለሩሲያ አጋርታ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ባለፈው ወር በሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ላይ ጥቃት ከመድረሱ ቀደም ብላ በሩሲያ ምድር ላይ ትልቆ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ሩሲያን አስጠንቅቃለች።
ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ መረጃ አላቸው ያላቸውን ሶስት ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው የኢራን ደህንነት ከሞስኮው አስከፊ ጥቃት ቀደም ብሎ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጸም የሚያመለክት መረጃ ለሞስኮ አጋርቷል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 22 የተቃጣው ይህ ጥቃት በሁለት አስርት አመታት ውስጥ በሩሲያ ምድር የተፈጸመ ከባድ ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል።
አውቶማቲክ መሳሪያ የታጠቁ አራት ታጣቂዎች በሙዚቃ ድግሱ ተሳታፊዎች ላይ የዘፈቀደ ተኩስ በመክፈት ከ130 በላይ ሰዎችን ገድለዋል።
ከኢራን በተጨማሪም አሜሪካም በሞስኮ የሽብር ጥቃት ይከሰታል የሚል ማስጠንቀቂያ ብታወጣም፣ ሞስኮ ግን የአሜሪካን አላማ በመጠራጠሯ አጣጥላው ነበር።
በኢራን እና በሞስኮ መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠንካራ በመሆኑ ኢራን አቅርባዋለች የሚባለው መረጃ ክብደት የሚሰጠው ነው።
ኢራን ባለፈው ጥሩ ወር በሞስኮ ጥቃት በማድረስ ኃላፊነት የወሰደው እና መቀመጫውን አፍጋኒስታን ያደረገው የአይኤስአይኤስ-ኮራሳን (አይኤስአይኤስ-ኬ) አባል የሆኑ 35 ግለሰቦችን መያዟ ይታወሳል።
ኢራን ግለሰቦቹን የያዘችው በኬርማን ከተማ በተከሰተው ፍንዳታ 100 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ኢራን ለሩሲያ የላከቸው ማስጠንቀቂያ ስለጊዜው እና ኢላማ ስለተደረገው ቦታ ዝርዝር ነገር ባይገልጽም፣ የሽብር ጥቃት ዝግጅት መኖሩ ላይ ትኩረት አድርጓል ተብሏል።
ይህ ኢራን ለሩሲያ አጋርታዋለች የተባለው መረጃ የአይኤስአይኤስ-ኬ አባላት ለዚሁ አላማ ሩሲያ መግባታቸውን እንደሚገልጽ ዘገባው ጠቅሷል።
ክሬሚሊን በዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም።
ጥቃቱን አድርሰዋል የተባሉት የታጂኪርታን ዜግነት ያላቸው አራት ግለሰቦች ተይዘው የሽብረተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ለጥቃቱም አይኤስአይኤስ-ኬ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል።
ነገርግን ፕሬዝደንት ፑቲን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ መግጫቸው ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወደ ዩክሬን ለማቅናት ሙከራ ማድረጋቸውን እና ከጥቃቱ ጀርባ ዩክሬን መኖሯን መግለጻቸው ይታወሳል።
የሩሲያ የፌደራል ሴኩሪቲ ሰርቪስ( ኤፍኤስቢ) አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) እና ዩክሬንን በሞስኮው ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ እጃቸው ሲል ከሷል።
ዩክሬን በዚህ ጥቃት እጇ እንደሌለበት አስተባብላች።