ኢራን እና አሜሪካ መልእክት መለዋወጣቸውን ቴህራን ገለጸች
ሚኒስትሩ እንዳሉት አሜሪካ ሄዝቦላ በጸረ-እስራኤል ጦርነት "ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፍ" ቴህራን እንድትጠይቅላት ጥያቄ አቅርባለች
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው እስራኤል በሀማስ ላይ እያደረገች ባለው አራት ወራትን ባስቆጠሰው ጦርነት ወቅት መልእክት ተለዋውጠዋል።
ኢራን እና አሜሪካ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ መልእከት መለዋወጣቸውን ቴህራን አስታውቃለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት እንደገለጸው እስራኤል በሀማስ ላይ እያደረገች ባለው አራት ወራትን ባስቆጠሰው ጦርነት ወቅት ስለሄዝቦላ ጉዳይ ጭምር መልእክት ተለዋውጠዋል።
"በዚህ ጦርነት እና ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የመልእክት መለዋወጥ ነበር" ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት አሜሪካ ሄዝቦላ በጸረ-እስራኤል ጦርነት "ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፍ" ቴህራን እንድትጠይቅላት ጥያቄ አቅርባለች።
ሄዝቦላ ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በእስራኤል-ሌባኖስ ድንበር ከባድ የተኩስ ልውውጥ አድርጓል፤ እስራኤል በሊባኖስ ላይ አጠቃላይ ጦርነት የምትከፍት ከሆነም እስከመጨረሻው እንደሚዋጋ መግለጹ ይታወሳል።
ሀማስ በጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ እና ከባድ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል እያካሄደች ያለችው የአጸፋ ጥቃት እስካሁን አልቆመም።
አሜሪካ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጆርዳን ውስጥ በኢራቅ እና ሶሪያ ድንበር አቅራቢያ የደረሰውን የሶስት ወታደሮቿን ግድያ ለመበቀል በሶሪያ እና በኢራቅ የወሰደችው ድብደባ ጦርነቱን ወደ ቀጣናው አስፍቶታል።
እስራኤል ከሊባኖስ ጋር ግጭት ውስጥ እንዳትገባ ሲሉ ያስጠነቀቁት አሚራብዶላሂያን ይህ የሚከሰት ከሆነ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "የመጨረሻ ቀን" ይሆናል ብለዋል።
ሚኒስትሩ የጋዛ ጦርነት መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ በድጋሚ እንዳያንሰራራ ሆኖ መደምሰስ እንዳለበት መግለጻቸው ይታወሳል።