ኢራን ወደ አየር ክልሏ የተጠጋን “የአሜሪካን የጦር አውሮፕላን አባረርኩ” አለች
የኢራን እና የአሜሪካ የሻከረ ግንኙነት በተለይ ባለፈው ዓመት የበለጠ ተባብሷል
ኢራን በኦማን ባህረሰላጤ የአሜሪካ ባህር ኃይል አውሮፕላኖች መታየታቸውን ተከትሎ አሜሪካን አስጠንቅቃለች
የኢራን የባህር ኃይል እሁድ በኦማን ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ የአሜሪካን "የስለላ አውሮፕላን" አግኝቼ አባረርኩ ብሏል።
"ከማስጠንቀቂያው በኋላ አውሮፕላኑ ያለፈቃድ ወደ ሀገሪቷ የአየር ክልል እንዳይገባ ተከልክሏል" ብሏል። አውሮፕላኑን የአሜሪካ ባህር ኃይል ኢፒ-3ኢ መሆኑንም ገልጿል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ኢራን ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ኃይሎች ጋር ተመሳሳይ ግጭቶች እንደነበራትም ዘገባው ጠቅሷል። እ.አ.አ በ2019 ኢራን በደቡባዊ ክፍሏ ላይ አገኘሁት ያለችውን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን መታለች።
ዋሽንግተን ለአጋሮቿ "ደህንነትን ለመጠበቅ" በነዳጅ አምራች ባህረ ሰላጤ ላይ የጦር መሳሪያ እና ወታደሮችን አሰማርታለች።
የኢራን እና የአሜሪካ የሻከረ ግንኙነት በተለይ ባለፈው ዓመት የበለጠ ተባብሷል። የ2015 የኒውክሌር ስምምነትን ለማደስ ንግግሮች ፍሬ እንዳላፈሩም ተነግሯል።
የአሜሪካ ማዕቀብ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች አቅርቦት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ ዋሽንግተን ከሩሲያ ጋር በተፈጠረ ግጭት በዩክሬን ውስጥ መሰረተ ልማቶችን ለማውደም ጥቅም ላይ እንደዋሉ ተናግራለች።
ኢራንም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ሩሲያ መላኳን አምናለች። ነገር ግን ከጦርነቱ በፊት የተላኩ ናቸው ብላለች።