አሜሪካ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፏን ልታቋርጥ እንደምትችል በደብዳቤ አስጠነቀቀች
ቴል አቪቪ በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ የሚገባበትን መንገድ በ30 ቀናት ውስጥ እንድታስተካክልም አሳስባለች
በአራት መተላለፊያዎች በየቀኑ ቢያንስ 350 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት ይኖርባቸዋል ብሏል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው
እስራኤል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ የሚገባበትን ሁኔታ ካላስተካከለች የተወሰኑ ወታደራዊ ድጋፎችን ልታቋርጥ እንደምትችል አሜሪካ አስጠነቀቀች።
ባለፈው እሁድ ለእስራኤል ተልኳል የተባለው የአሜሪካ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እስራኤል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ መከልከሏን አልያም እንቅፋት መሆኗን ያሳያል።
ቴል አቪቭ በመስከረም ወር ብቻ 90 በመቶ የሚሆን ከሰሜን ወደ ደቡባዊ ጋዛ የሚደረግ የሰብአዊ ድጋፍ እንቅስቃሴ ማወኳንም ጠቁሟል።
በሰሜናዊ ጋዛ ድብደባዋን ያጠናከረችው እስራኤል በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና በመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን ተፈርሟል የተባለውን ደብዳቤ እና የአጋሯን ስጋት “በአንክሮ እየተመለከተችው ነው” ብሏል አክሲዮስ የተባለው ድረገጽ በዘገባው።
የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ ያጠናከረው ጥቃት የሃማስ ይዞታዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑንና የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ አለመከልከሉን ቢገልጽም በርካታ ንጹሃን ተገድለው የሰብአዊ ቀውሱም እየከፋ መሄዱን የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ገልጸዋል።
እስራኤል ከትናንት በስቲያ ሰኞ የአለም የምግብ ድርጅት ድጋፍን የጫኑ 30 ተሽከርካሪዎች በኤሪዝ መተላለፊያ በኩል ወደ ጋዛ መግባታቸውን አስታውቃለች።
የመንግስታቱ ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ ከ400 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን አስቸኳይ ድጋፍ ቢሹም እስራኤል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ የፈቀደችው ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው ብሏል።
አሜሪካ ለእስራኤል በጻፈችው ደብዳቤም በጋዛ ያለው የሰብአዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁሟል።
እስራኤል በ30 ቀናት ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ በሚገባ እንዲገባ ካላደረገች እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ይላል ደብዳቤው።
የአሜሪካ ህግ የሀገሪቱን ሰብአዊ ድጋፍ ለሚገባቸው ወገኖች እንዳይደርስ ለሚያደርጉ መንግስታት የወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጥ እንደሚገባ እንደሚያዝም ጠቅሷል።
እስራኤል ሰሜናዊ ጋዛን “ከማግለል ተቆጥባ” በአራት ዋናዋና መተላለፊያዎች በየቀኑ ቢያንስ 350 ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፍቀድ እንዳለባትም ነው ያሳሰበው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር “ደብዳቤው ሚስጢራዊ የዲፕሎማሲያዊ ንግግር ስለሆነ ዝርዝሩን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አንፈልግም” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ የሚቀርብባትን ወቀሳ የማትቀበለው እስራኤልም ስለደብዳቤው እስካሁን በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም።
ቴል አቪቭ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ሰብአዊ ድጋፎችን ማከፋፈል ላይ ድክመት እንዳለባቸውና ሃማስ እርዳታ እየዘረፈ መሆኑን በመጥቀስ ውንጀላውን ስትቃወም መቆየቷ ይታወሳል።