ኢራንና ሩስያ ለ20 አመት የሚቆይ የወታደራዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
የሩስያና ኢራን አዲስ የአጋርነት ስምምነት ምዕራባውያን በስጋት እንደተመለከቱት ተገልጿል
በሩሲያ ጉብኝት ያደረጉት የኢራኑ ፕሬዝዳንት ከሩስያ አቻቸው ጋር በተለያዩ ቀጠናዊና ሁለትዮሽ አጋርነቶች ዙርያ መክረዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የኢራኑ አቻቸው መሱድ ፔዜሽኪያን የ20 ዓመታት ስትራቴጂካዊ አጋርነት በመፈራረም በሀገራቸው መካከል ያለውን ወታደራዊ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሩሲያ እና ኢራን በደህንነት መረጃዎች እና አገልግሎቶች ፣በወታደራዊ ልምምድ ፣የጦር መርከብ ልምምድ እና የጋራ ወታደራዊ መኮንኖች ስልጠናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ያሳድጋሉ።
በተጨማሪም ሁለቱም አንድኛውን ሀገር ለማጥቃት ለሚውል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ግዛታቸውን ላለመፍቀድ ፣ አንዳቸውን ሀገር ለሚያጠቃ ወራሪ ሀይል አገዛ እና እውቅና ላለመስጠትእንዲሁም ወታደራዊ ስጋቶችን ለመከላከል በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
ነገር ግን በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል በተደረገው ስምምነት ውስጥ የተካተተውን ዓይነት የጋራ መከላከያ አንቀጽ አላካተተም።
እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ ቴክኒካል ትብብርን እንደሚያሳድጉ ቢናገሩም በተለይ አሜሪካ እና አጋሮቿ የሚያሳስባቸው የጦር መሳሪያ ልውውጥ እና ዝውውሮች ጉዳይ የተጠቀሰ ነገር የለም።
ሆኖም ይህኛው የ20 አመት ስትራቴጂካዊ ስምምነት በምዕራባውያን አይን በስጋት የታየ ነው፡፡
ኢራን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለምትሰነዘረው ጥቃት ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ትሰጣለች ሲሉ ይከሳሉ።
ሞስኮ እና ቴሄራን በበኩላቸው የእነርሱ የቅርብ ግንኙነት በሌሎች ሀገራት ላይ ያነጣጠረ አይደለም በሚል ያስተባብላሉ፡፡
ሩሲያ ከዚህ ቀደም ለኢራን የኤስ-300 የአየር መከላከያ ሚሳይል ቴክኖሎጂን ስታቀርብ የቆየች ሲሆን ኢራን የሩሲያ ተዋጊ ጄቶችን ለማግኘት ፍላጎት እንዳላት መረጃዎች መውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በላፈው ሀምሌ ወር የኢራን ፕሬዝዳንትነትን ቦታ የተረከቡት መሱድ ስምምነቱን “የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ጠቃሚ አዲስ ምዕራፍ ነው” ሲሉ አወድሰውታል፡፡
ሞስኮ እና ቴሄራን በርካታ የሚጋሯቸው ጉዳዮች እንዳሉ የገለጹት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ከወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት በዘለለ ሁለቱ ሀገራ በራሳቸው ገንዘብ በመገበያየት ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
“የምዕራባውያን ሀገራት ማዕቀቦች እና የበላይነትን ማስጠበቅ ሩጫ በመድረኩ የተለየ ድምጽ ያላቸው ሀገራት ወደ ፊት እንዲወጡ የሚያስገድድ ነው” ያሉት ፑቲን የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት የዚህ ምሳሌ እድርገው አቅርበዋል፡፡
ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ባለፈ በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ መክረዋል የበሽር አላሳድ መንግስ ዋነኛ ደጋፊ የነበሩት ኢራን እና ሩስያ የአሳድ መንግስት ውድቀት በቀጠናው ባላቸው ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ መገምገማቸውንም ክሪምሊን ገልጿል፡፡