በኢራን የኒውክሌር ጣብያ መሳሪያዎች ላይ እስራኤል የቀበረቻቸው ፈንጂዎች መገኘታቸው ተነገረ
ኢራን በመጪው ጊዜ የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ልታደርግ እንደምትችል ይነገራል
የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት ጃቫድ ዛሪፍ አለምአቀፍ ጫናዎች ቴሄራን ለእስራኤል ጥቃት ተጋላጭ እንድትሆን አድርገዋል ብለዋል
የእስራል የስለላ ኤጂንሲዎች ለኢራን የኒውክሌር መርሀ ግብር አገልግሎት ለመስጠት በተገዙ መሳሪያዎች ላይ ፈንጂዎችን በድብቅ አስቀምጠው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ፈንጂዎቹ የተለያዩ ፈሳሽ ኬሚካሎችን ለማጣራት እና ለመለየት አገልግሎት በሚሰጡ “ሴንትሪፉውጅ” በተባሉ መሳሪያዎች ላይ ተደብቀው መገኝታቸውን የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጃቫድ ዛሪፍ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ዋና ተደራዳሪ ስለ ክስተቱ እና ስለተፈጠረበት ጊዜ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኢራንን የኒውክሌር መርሀ ግብር ለማስተጓጎል ቁልፍ በሆኑ ማዕከላት ላይ እና ታዋቂ የኒውክሌር ሳይንቲስቶችን በመግደል ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዛሪፍ የተሳካው የእስራኤል “ሰርጎገብነት” በሀገሪቱ ላይ የተጣሉት አለምአቀፋዊ ማዕቀቦች የፈጠሩት ተጋላጭነት ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ዛሪፍ ከሀገር ውስጥ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ይህ ማዕቀቡ ያስከተለው ጉዳት ነው የምርምምር መሳሪያዎችን በቀጥታ ከአምራቾቹ ከመግዛት ይልቅ ከማዕቀቡ ተደብቀን በሶስተኛ ወገን የምንፈጽማቸው ግዢዎች መሰል አደገኛ ችግሮችን ይፈጥራሉ” ነው ያሉት፡፡
እስራኤል በግዢ ሰንሰለት ውስጥ ከሚገኙ አንዳቸው ጋር እንኳን ግንኙነትን መመስረት ከቻለች ከዚህ የከፋ ጉዳት ልታስከትል እንደምትችልም አሳስበዋል፡፡
የኢራን “ሴንትሪፉውጅ” የተባሉት መሳሪያዎች ግዢ ሀገሪቱ ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ የሚውል ዩራኒየምን ለማምረት ያግዛል በሚል ከፍተኛ አለም አቀፋዊ ውግዘት ይቀርብበታል፡፡
ቴሄራን በአንጻሩ የኒውክሌር መርሀገብሯ ለግብርና ፣ ለሀይል እና ህክምና ዘርፎች ላይ ከመጠቀም ባለፈ ጦር መሳሪያ የማምረት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ትገልጻለች፡፡
በስለላ ድርጅቶች እና በተለያዩ መንገዶች የሚፈጸሙ የእስራኤል ሚስጥራዊ ዘመቻዎች ከኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እንደሚያልፍ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ የቀድሞውን የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬን ለመግደል የኢራን ሰላዮችን በመመልመል ከቴህራን በስተሰሜን በሚገኝ የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ቦምብ እንዲቀብሩ ማድረጋቸውንም አስታውሷል፡፡