የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከሁቲ ቃልአቀባይ ጋር መከሩ
በኦማን መዲና ሙስካት የተካሄደው ምክክር ቴህራን በእስራኤል ሊፈጸምባት ለሚችል ጥቃት በሚወሰድ አጻፋ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገምቷል
ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ሳኡዲ፣ ኳታር እና ኢራቅ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከየመኑ ሁቲ ቃልአቀባይ ሞሀመድ አብዱልሳላም ጋር ተወያዩ።
ለይፋዊ ጉብኝት ኦማን የገቡት ሚኒስትሩ ቴህራን ድጋፍ ታደርግለታለች ከሚባለው ሁቲ ቃል አቀባይ ጋር በወቅታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ፍጥጫ ዙሪያ መምከራቸውን የኢራኑ ፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ለሁቲ ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃንም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የቡድኑን ቃልአቀባይ መገናኘት ቢዘግቡም የምክክሩን ዝርዝር ይፋ አላደረጉም።
እስራኤል በጥቅምት ወር መጀመሪያ በኢራን ለተፈጸመባት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት እወስደዋለው ያለችው የአጻፋ ምላሽ በሚጠበቅበት ወቅት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ በቀጠናው ጉብኝት እያደረጉ ነው።
አባስ አራግቺ በሳኡዲ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኳታር እና ኦማን ያደረጓቸው ጉብኝቶችም ውጥረቱን ለማርገብ ያለመ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
ከእስራኤል ጋር ቀጠናዊ ጦርነት ውስጥ መግባት አልፈልግም የምትለው ቴህራን የባህረሰላጤው ሀገራት ለቴል አቪቭ የአየር ክልላቸውን ክፍት እንዳያደርጉ ስታሳስብ ቆይታለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ይህንኑ ለማጠናከር ያለመ ነው የተባለ ሲሆን፥ አጋሮችን የማሰባሰብ አላማ ማንገቡም ተዘግቧል።
ከሁቲ ቃል አቀባይ ጋር የተደረገው ውይይትም ቴህራን በቀጠናው የምታስታጥቃቸው ሀይሎች በእስራኤል ላይ ሊወስዱት ስለሚችሉት ጥቃት የተመከረበት ሊሆን እንደሚችል ነው የተገመተው።
በሊባኖስ ድጋፍ የምታደርግለት ሄዝቦላህ መሪዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ባሻገር የቡድኑን አቅም የማዳከም የእስራኤል የማያባራ ጥቃት ያሳሰባት ኢራን፥ በየመን፣ ሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙ ታጣቂዎች ወደ ሊባኖስ እንዲያቀኑ ስለማድረጓ ባለፈው ወር ተዘግቦ ነበር።
40 ሺህ የሚጠጉ ታጣቂዎች ሄዝቦላህን ለማገዝ ወደ ሊባኖስ አምርተዋል ቢባልም እስካሁን ቡድኑን ተቀላቅለው ድጋፍ ስለማድረጋቸው ግን አልታወቀም።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በኢራን ላይ የሚወሰደው የአጻፋ እርምጃ አይቀሬ መሆኑን አመላክቷል።
ይሁን እንጂ የኢራን የነዳጅና ኒዩክሌር ጣቢያዎች የጥቃት ኢላማ እንደማይሆኑ የእስራኤል ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
ቴህራንም ለተጠባቂው የእስራኤል እርምጃ ምላሽ ለመስጠት በመካከለኛው ምስራቅ ከምታስታጥቃቸው ሃይሎች ጋር እየተነጋገረች ነው ተብሏል።