ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ቻይና እና ኢራን በዩክሬኑ ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈዋል በሚል የምዕራባውያኑ ጫና በርትቶባቸዋል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በቻይና የሶስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ቤጂንግ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትሮቻቸውን ያካተተ ልኡክን እየመሩ ነው ቤጂንግ የገቡት።
ራይሲ ከ22 አመቷ ማሻ አሚኒ ግድያ በኋላ የተቀሰቀሰውን አመጽ በድል ተወጥተነዋል ባሉ ማግስት ነው ቻይናን እየጎበኙ ያሉት።ይህም ከ20 አመት በኋላ ቻይናን የጎበኙ የኢራን ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል።
ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና ሌሎች የቻይና ከፍተኛ የቻይና ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ የሚጠበቁት ፕሬዝዳንቱ፥ በበርካታ ዘርፎች የትብብር ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ የኢራኑ የዜና አገልግሎት ኢርና ዘግቧል።
በ2021 የ25 አመት “ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት” የተፈራረሙት ቻይና እና ኢራን ጠንካራ የንግድ ግንኙነት አላቸው።
ባለፉት 10 ወራት እንኳን ኢራን ወደ ቻይና ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶቿን ልካለች፤ በአንጻሩ ቴህራን 12 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው ምርቶችን ከቤጂንግ አስገብታለች።
የምዕራባውያን ጫና
ኢራን እና ቻይና በኒዩክሌር እና የንግድ ማዕቀቦች ከምዕራባውያን ጋር መካሰስ ውስጥ ከገቡ አመታት ተቆጥረዋል።
በተለይ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሞስኮ ጎን ተሰልፈዋል በሚል ጫናው በርትቶባቸዋል።
ቴህራን ለሞስኮ ድሮኖችን ሰጥታለች የሚለው ዜና ከተደመጠ በኋላም ምዕራባውያን ማዕቀቦችን ለመጣል ሲዝቱ መቆየታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታውሷል።
ቤጂንግም በጸጥታው ምክር ቤት ጭምር በሩሲያ ላይ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦችን ወድቅ በማድረግ ለሞስኮ ድጋፏን ችራለች በሚል ትወቀሳለች።
ኢራንም ሆነች ቻይና ግን የምዕራባውያኑን ወቀሳ አይቀበሉትም፤ ለሞስኮ ወታደራዊ ድጋፍ አላደረግንም፤ ሀገራቱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጦርነቱን እንዲያስቆሙ ግን እንደግፋለን ሲሉም ይደመጣሉ።
የምዕራባውያኑን ማዕቀቦችም “በስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት” ለማለፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የቻይና ጉብኝትም ይህንኑ ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ተናግረዋል።