የደህንነት ሹሙ በእስራኤል የሚቃጡ ጥቃቶችን ለማምከን አለመቻላቸውን ተከትሎ ማባረራቸው ተነግሯል
ኢራን በእስራኤል እንደተፈጸሙ ከሚታሰቡ ተከታታይ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የደህንነት ሹሟን ከኃላፊነት አነሳች፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የደህንነት ሹም የነበሩት ሁሴን ጣዒብ ከኃላፊነት የተነሱት ቱርክ የኢራን ደህንነቶች ናቸው ያለቻቸውን 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተከትሎ ነው፡፡
ሰዎቹ ቱርክ በሚገኙ እስራኤላውያን ላይ ጉዳት የማድረስ ውጥን እንደነበራቸው ተነግሯል፡፡ እስራኤልም ቀደም ብላ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያዎችን ስትሰጥ ነበረ፡፡
አንካራ በአራት የተለያዩ ቡድኖች የተደራጁት ኢራናውያኑ ደህንነቶች ግድያዎችን ጭመር የመፈጸም ውጥን እንደነበራቸው ነው ያስታወቀችው፡፡
ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻልና አምባሳደሮችን ጭመር ለመሰየም መስማማቷ ይታወሳል፡፡
ኢራን እና እስራኤል የጎሪጥ መታየት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት በባለስልጣናትና ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች ደግሞ ይበልጥ አቃቅሯቸዋል፡፡
የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ ከነበሩት ቃሲም ሱሉይማኒ ግድያ ጀርባ እጇ አለበት በሚል እስራኤልን የምትከሰው ኢራን በቅርቡ በተፈጸሙ ተከታታይ ግድያዎች እና በኒውክሌር ማብለያ ጣቢያዎቿ ከሚቃጡ ጥቃቶች ጀርባ እጇ አለበት ስትልም ትገልጻለች፡፡
ግድያዎቹንና ሌሎቹንም በእስራኤል ይፈጸማሉ የሚባሉ ሻጥሮችን ማክሸፍ አልቻሉም በሚልም ነው የደህንነት ሹሙ ከኃላፊነት የተነሱት፡፡
ምናልባትም የአብዮት ዘቡ አዛዥ የደህንነት አማካሪ ሆነው ሊሾሙ እንደሚችሉም ከቴህራን የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡