ማሳሰቢያው የኢራን ደህንነቶች ቱርክ የሚገኙ የእስራኤል ዜጎችን ሊያጠቁ ይችላሉ በሚል የተሰጠ ነው
እስራኤል ዜጎቿ በቶሎ ቱርክን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች፡፡
ማሳሰቢያው የኢራን ደህንነቶች ቱርክ የሚገኙ የእስራኤል ዜጎችን ሊያጠቁ ይችላሉ በሚል የተሰጠ ነው፡፡
ማሳሰቢያውን የሰጡት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬይር ላፒድ እስራኤላውያን በተቻላቸው ፍጥነት ኢስታንቡልን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከሰሞኑ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የበለጠ ውጥረት እየነገሰ ነው፡፡ በዩራኒየም ማብለያ የኒውክሌር ጣቢያዎቼ እና በጦር መሪዎቼ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጀርባ እስራኤል አለች ስትል የከሰሰችው ኢራን የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ በሚል ስትይዝ ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬይር ላፒድም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይመስላል ማሳሰቢያውን የሰጡት፡፡ የኢራን ደህንነቶች ከአሁን ቀደም በእስራኤል ዜጎች ላይ በበዓል የመዝናኛ ቀናት የጥቃት ሙከራዎችን ማድረጋቸውን በማስታወስ ኢስታንቡልን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል፡፡
“ኢስታንቡል ከሆናችሁ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ” ሲሉም ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተናገሩት፡፡
ወደ ኢስታንቡል ለመጓዝ ያሰቡ ጉዟቸውን እንዲሰርዙም አሳበዋል፤ ተዝናኖቱ ህይወታቸውን እንደማይተካ በመጠቆም፡፡
ከፓርቲያቸው የሽ አቲድ ህግ አውጭዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ የግድ ካልሆነ በስተቀር ወደ ቱርክ እንዳትጓዙ ሲሉም ነው የሃገራቸውን ዜጎች ያስጠነቀቁት፡፡
ማስጠንቀቂያውን በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከኢራንም ሆነ ከቱርክ የተሰጠ መልስ የለም፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ እጅግ ተቃርባለች ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡